2 ዜና መዋዕል 26 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ዖዝያን መንገሡ 1 የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ የዐሥራ ስድስት ዓመት ዕድሜ የነበረውን ዖዝያንን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሡት። 2 ንጉሡም ከአባቶቹ ጋር ከአንቀላፋ በኋላ ዖዝያን ኤላትን ሠራ፥ ወደ ይሁዳም መለሳት። 3 ዖዝያንም መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ኀምሳ ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 4 አባቱም አሜስያስ እንዳደረገው ሁሉ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ። 5 ጌታንም መፍራት ባስተማረው ዘካርያስ በእርሱም ዘመን ጌታን ለመፈለግ ልቡን አቀና፤ ጌታንም በፈለገ ጊዜ ጌታ ነገሩን አከናወነለት። 6 ወጥቶም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተዋጋ፥ የጌትንና የየብናን የአዞጦንንም ቅጥር አፈረሰ፤ በአዛጦንና በፍልስጥኤማውያንም አገር ከተሞችን ሠራ። 7 እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያንና በጉርበኣል በሚኖሩ ዓረባውያን በምዑናውያንም ላይ ረዳው። 8 አሞናውያንም ለዖዝያን ገበሩ፤ እጅግም በርትቶ ነበርና ዝናው እስከ ግብጽ መግቢያ ድረስ ተሰማ። 9 ዖዝያንም በኢየሩሳሌም በማዕዘኑ በርና በሸለቆው በር ቅጥሩም በዞረበት ማዕዘን አጠገብ ግንቦችን ሠርቶ መሸጋቸው። 10 ብዙም እንስሶች ነበሩትና በምድረ በዳውና በቈላው በደጋውም ግንብ ሠራ፥ ብዙ ጉድጓድም ማሰ፤ ደግሞም እርሻ ይወድድ ነበርና በተራራማውና በፍሬያማው ስፍራ አራሾችና አትክልተኞች ነበሩት። 11 ደግሞም ለዖዝያን በሠራዊቱ ውስጥ ለውግያ ብቁ የሆኑ ወታደሮች ነበሩት፤ በንጉሡ አለቃ በሐናንያ ትእዛዝ በአለቃው በመዕሤያና በጸሐፊው በይዒኤል እጅ እንደ ተቈጠሩ ወደ ሰልፍ በየቁጥራቸው ይወጡ ነበር። 12 የአባቶቻቸውም ቤቶች አለቆች የጽኑዓን ኃያላኑ ቍጥር ሁሉ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበር። 13 ንጉሡንም በጠላቱ ላይ እንዲያግዝ፥ በታላቅ ኃይል ወደ ጦርነት የሚወጣ፥ በትእዛዛቸው ሥር የነበረ ሠራዊት ሦስት መቶ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበረ። 14 ዖዝያንም ለሠራዊቱ ሁሉ ጋሻና ጦር፥ ራስ ቁርና ጥሩር፥ ቀስትና የሚወነጭፉትን ድንጋይ አዘጋጀላቸው። 15 በኢየሩሳሌምም በብልሃተኞች እጅ የተሠሩትን፥ በግንብና በቅጥር ላይ የሚቀመጡትን፥ ፍላጻና መርግ የሚወረወርባቸውን መሣሪያዎች ሠራ፤ እስኪበረታም ድረስ እግዚአብሔር በድንቅ ረድቶታልና ዝናው እስከ ሩቅ አገር ድረስ ተሰማ። ትዕቢትና ከዳተኝነት 16 ነገር ግን በበረታ ጊዜ ለጥፋት ልቡ ታበየ፥ አምላኩንም ጌታን በደለ፤ ወደ ጌታ መቅደስ ገብቶ በዕጣን መሠዊያ ላይ ዐጠነ። 17 ካህኑም ዓዛርያስ ከእርሱም ጋር ጽኑዓን የነበሩ ሰማኒያ የጌታ ካህናት ተከትለውት ገቡ። 18 ንጉሡንም ዖዝያንን እየተቃወሙ እንዲህ አሉት፦ “ዖዝያን ሆይ! ዕጣን ማጠን የተቀደሱት የአሮን ልጆች የካህናቱ ሹመት ነው እንጂ ለጌታ እንድታጥን ለአንተ አይገባህም፤ በድለሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከአምላክህም ከጌታ ዘንድ ክብር አያስገኝልህም።” 19 ዖዝያንም ተቈጣ፤ የሚያጥንበትም ጥና በእጁ ነበረ፤ ካህናቱንም በተቈጣ ጊዜ በካህናቱ ፊት በጌታ ቤት ውስጥ በዕጣኑ መሠዊያ አጠገብ ሳለ በግምባሩ ላይ ለምጽ ታየ። 20 ታላቁም ካህን ዓዛርያስ ካህናቱም ሁሉ ተመለከቱት፥ እነሆም፥ በግምባሩ ላይ ለምጽ ነበረ፤ ፈጥነውም እንዲወጣ አስገደዱት፥ እርሱም ደግሞ ጌታ ቀሥፎት ነበርና ለመውጣት ቸኮለ። 21 ንጉሡም ዖዝያን እስኪሞት ድረስ ለምጻም ነበረ፤ ለምጻምም ሆኖ ከጌታ ቤት ተነጥሎአልና በተለየ ቤት ይቀመጥ ነበር፤ ልጁም ኢዮአታም በንጉሡ ቤት ላይ ሆኖ በምድሩ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ነበር። 22 የቀረውንም የፊተኛውንና የኋለኛውን የዖዝያንን ነገር ነቢዩ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ጽፎታል። 23 ዖዝያንም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ እነርሱም፦ “ለምጻም ነው” ብለው ከአባቶቹ ጋር በነገሥታቱ መቃብር እርሻ ውስጥ ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፋንታ ነገሠ። |