ሮሜ 8:15 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እንደገና የፍርሃት ባርያ የሚያደርጋችሁን መንፈስ አልተቀበላችሁምና፥ ነገር ግን “አባ! አባት!” ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብላችኋል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እንደ ገና የፍርሀት ባሪያ የሚያደርጋችሁን መንፈስ ሳይሆን፣ “አባ፣ አባት” ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብላችኋልና፤ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ስለዚህ “አባ! አባታችን ሆይ!” ብላችሁ የምትጠሩበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ በፍርሃት ለመኖር እንደገና የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁም። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ዳግመናም አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደ ገና ለፍርሀት የባርነት መንፈስን አልተቀበላችሁምና። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። |
እኔ ግን፦ “‘ከወንዶች ልጆች ጋር እንዴት አስቀምጥሻለሁ? ያማረችውንስ ምድር እጅግ የከበረችውን የአሕዛብን ርስት እንዴት እሰጥሻለሁ? ብዬ ነበር። ደግሞ፦ አባቴ ብለሽ ትጠሪኛለሽ፤ እኔንም ከመከተል አትመለሽም ብዬ ነበር።
ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በማናቸውም ጊዜ ስትጸልዩ እንዲህ በሉ፦ ‘በሰማያት የምትኖር አባት ሆይ! ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤
ኢየሱስንም ባየ ጊዜ ጮኾ በፊቱ ተደፋ፤ በታላቅ ድምፅም፦ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ! አንተ ከእኔ ጋር ምን አለህ? እንዳታሰቃየኝ እለምንሃለሁ፤” አለ።
በጌርጌሴኖንም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች የሚኖረው ሕዝብ ሁሉ በታላቅ ፍርሃት ተይዘው ስለ ነበር ከእነርሱ እንዲሄድ ለመኑት፤ እርሱም በታንኳ ገብቶ ተመለሰ።
ኢየሱስም “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ ‘እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ፤’ ብለሽ ንገሪአቸው፤” አላት።
ፍጥረት ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን እኛ ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት በናፍቆት እየተጠባበቅን እኛ ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን።
እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ይረዳናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ያማልድልናል፤
ምክንያቱም አንዱ መጥቶ እኛ ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ሆኖ ብታገኙት፥ በመልካምነታችሁ ትታገሡታላችሁ።