ኃያል ሆይ፥ በክፋት ለምን ትኩራራለህ? ሁልጊዜስ በመተላለፍ?
ከበጎ ነገር ይልቅ ክፋትን፣ ጽድቅን ከመናገር ይልቅ ዐመፃን ወደድህ። ሴላ
ከደግነት ይልቅ ክፋትን፥ ከእውነት ይልቅ ሐሰትን ትመርጣለህ።
ሁሉ ተካክሎ በአንድነት በደለ፤ አንድ ስንኳ በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም።
እስከ መቼ በሰው ላይ ትነሣላችሁ? እናንተ ሁላችሁ እንዳዘነበለ ግድግዳ እንደ ፈረሰም ቅጥር ትገድላላችሁ።
የኀጥእ ነፍስ ክፉን ትመኛለች፥ በፊቱም ባልንጀራው ሞገስን አያገኝም።
“ሕዝቤ ሰንፈዋልና አላወቁኝም፤ ሰነፎች ልጆች ናቸው፥ ማስተዋልም የላቸውም፤ ክፉ ነገርን ለማድረግ ብልሃተኞች ናቸው፥ በጎ ነገርን ማድረግ ግን አያውቁም።”
ምላሳቸው የተሳለ ፍላጻ ነው፤ ሽንገላን ይናገራሉ፤ ሰው ከባልንጀራው ጋር በሰላም ይናገራል፥ በልቡ ግን ያደባበታል።
መልካሙን የምትጠሉ፥ ክፉውን የምትወዱ፤ ቁርበታቸውን ከላያቸው ላይ ገፈፋችሁ፥ ሥጋቸውንም ከአጥንታቸው ለያያችሁ፤
እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከእራሱ አፍልቆ ነው፤ ሐሰተኛ፥ የሐሰትም አባት ነውና።
የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ለወጡ፤ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡርን አመለኩ አገለገሉትም፤ እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም የተባረከ ነው፤ አሜን።
ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተወጠሩ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ፥
ውሻዎችና አስማተኞች፥ ሴሰኛዎችም፥ ነፍሰ ገዳዮችም፥ ጣዖት አምላኪዎችም፥ ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ ይቀራሉ።