መዝሙር 52 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 52 ለመዘምራን አለቃ፤ ኤዶማዊው ዶይቅ ወደ ሳኦል መጥቶ፣ “ዳዊት ወደ አቢሜሌክ ቤት መጥቷል” ብሎ በነገረው ጊዜ፤ የዳዊት ማስኪል። 1 ኀያል ሆይ፤ በክፋት ለምን ትኵራራለህ? አንተ በእግዚአብሔር ዐይን የተናቅህ፣ እንዴትስ ዘወትር ትታበያለህ? 2 አንተ ማታለልን ሥራዬ ብለህ የያዝህ፤ አንደበትህ እንደ ሰላ ምላጭ፣ ጥፋትን ያውጠነጥናል። 3 ከበጎ ነገር ይልቅ ክፋትን፣ ጽድቅን ከመናገር ይልቅ ዐመፃን ወደድህ። ሴላ 4 አንተ አታላይ አንደበት ሆይ፤ ጐጂ ቃላትን ሁሉ ወደድህ! 5 እግዚአብሔር ግን ለዘላለም ያንኰታኵትሃል፤ ይነጥቅሃል፤ ከድንኳንህም መንጥቆ ያወጣሃል፤ ከሕያዋንም ምድር ይነቅልሃል። ሴላ 6 ጻድቃን ይህን አይተው ይፈራሉ፤ እንዲህ እያሉም ይሥቁበታል፤ 7 “እግዚአብሔርን መጠጊያ ያላደረገ፣ ነገር ግን በሀብቱ ብዛት የተመካ፣ በክፋቱም የበረታ፣ ያ ሰው እነሆ!” 8 እኔ ግን በእግዚአብሔር ቤት፣ እንደ ለመለመ የወይራ ዛፍ ነኝ፤ ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ በእግዚአብሔር ምሕረት እታመናለሁ። 9 ስላደረግኸው ነገር ለዘላለም አመሰግንሃለሁ፤ ስምህ መልካም ነውና፣ ስምህን ተስፋ አደርጋለሁ፤ በቅዱሳንም መካከል አመሰግንሃለሁ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.