መዝሙር 52 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእግዚአብሔር ፍርድና የእግዚአብሔር ጸጋ 1 አንተ ብርቱ ሰው፥ በእግዚአብሔር ወገኖች ላይ ክፉ ነገር በማድረግ የእግዚአብሔር ፍቅር ዘለዓለማዊ መሆኑን እያወቅህስ ስለምን ዘወትር ትመካለህ? 2 አንተ ተንኰለኛ ጥፋትህን ታሤራለህ፤ አንደበትህ እንደ ተሳለ ምላጭ ነው። 3 ከደግነት ይልቅ ክፋትን፥ ከእውነት ይልቅ ሐሰትን ትመርጣለህ። 4 አንተ አታላይ ሰው ሰዎችን የሚጐዳ ቃል መናገር ትወዳለህ! 5 ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘለዓለሙ ያጠፋሃል፤ ከቤትህ አስወጥቶ ያባርርሃል። ከሕያዋንም ምድር ያስወግድሃል። 6 የእግዚአብሔር ሰዎችም ይህን አይተው ይፈራሉ፤ እንዲህ እያሉ ይሳለቃሉ፤ 7 ሌሎችን በማጥፋት ብርቱ የሆነ፥ በታላቅ ሀብቱ የተመካና፥ ብርታቱን በእግዚአብሔር ላይ ያላደረገ ሰው ይኸውላችሁ። 8 እኔ ግን በእግዚአብሔር ቤት እንደ ለምለም የወይራ ዛፍ ነኝ፤ በማያቋርጥ ፍቅሩም፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም እታመናለሁ። 9 አምላክ ሆይ! ስላደረግኸው መልካም ነገር ሁሉ ለዘለዓለም አመሰግንሃለሁ፤ በአማኞች ፊት ቆሜ ስለ አንተ ቸርነት እናገራለሁ። |