ነህምያ 5:12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እነርሱም፦ “እንመልስላቸዋለን፥ ከእነርሱም ምንም አንፈልግም፤ አንተ እንዳልኸው እናደርጋለን” አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ ቃል እንደገቡት እንዲያደርጉ አስማልኳቸው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እነርሱም፣ “እንመልሳለን፤ ምንም ዐይነት ትርፍ አንጠይቃቸውም፤ እንዳልኸን እናደርጋለን” አሉ። ካህናቱን ጠራኋቸው፤ መኳንንቱንና ሹማምቱም የገቡትን ቃል እንዲፈጽሙ አማልኋቸው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም መሪዎቹም “እንዳዘዝከን እናደርጋለን፤ የተወሰደባቸውን ሀብትና ንብረት ሁሉ እንመልስላቸዋለን፤ የተበደሩትንም ዕዳ ክፈሉ ብለን አንጠይቃቸውም” ሲሉ መለሱልኝ። እኔም ካህናቱን ወደ ውስጥ ጠርቼ፥ መሪዎቹ የገቡትን ቃል ይፈጽሙ ዘንድ እንዲያስምሉአቸው አደረግሁ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እነርሱም፥ “እንመልስላቸዋለን፤ ከእነርሱም ምንም አንሻም፤ እንደተናገርህ እንዲሁ እናደርጋለን” አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ እንደዚህ ነገር ያደርጉ ዘንድ አማልኋቸው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እነርሱም፦ እንመልስላቸዋለን፥ ከእነርሱም ምንም አንሻም፥ እንደ ተናገርህ እንዲሁ እናደርጋለን አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ እንደዚህ ነገር ያደርጉ ዘንድ አማልኋቸው። |
የቀሩት ሕዝብ፥ ካህናቱ፥ ሌዋውያኑ፥ በር ጠባቂዎቹ፥ መዘምራን፥ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች፥ ከምድር ሕዝቦች ወደ እግዚአብሔር ሕግ ራሳቸውን የለዩ ሁሉ፥ ሚስቶቻቸው፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው፥ የሚያውቁትና የሚያስተውሉት ሁሉ፥
ከወንድሞቻቸውና ከመኳንንቶቻቸው ጋር በመሆን በእግዚአብሔር ባርያ በሙሴ እጅ በተሰጠው በእግዚአብሔር ሕግ ለመሄድ፥ የጌታ አምላካችንን ትእዛዞቹን ሁሉ፥ ፍርዶቹንና ሥርዓቶቹን ለመጠበቅና ለማድረግ ወደ እርግማንና መሐላ ገቡ።
ከእነርሱም ጋር ተከራከርሁ፥ ረገምኋቸውም፥ ከእነርሱም አያሌዎቹን መታሁ፥ ጠጉራቸውንም ነጨሁ፥ እንዲህም ብዬ በእግዚአብሔር አማልኋቸው፦ ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለእናንተና ለልጆቻችሁ አትውሰዱ።
በብድር የያዛችሁትን እርሻቸውን፥ የወይን ቦታቸውን፥ ወይራቸውን፥ ቤታቸውን፥ ከመቶ አንድ የወሰዳችሁትን ብር፥ እህሉን፥ አዲሱን ወይን ጠጅና ዘይት እባካችሁ ዛሬ መልሱላቸው።”
ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን “ጌታ ሆይ! ካለኝ ሁሉ እኩሌታውን ለድኾች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ፤” አለው።