ዕዝራ 10 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የሕዝቡ መልስ 1 ዕዝራ በእግዚአብሔር ቤት ፊት በግንባሩ ወድቆ እያለቀሰ በሚጸልይበትና በሚናዘዝበት ጊዜ፤ ወንዶች፥ ሴቶችና ሕፃናት የሚገኙበት እጅግ ታላቅ ጉባኤ ወደ እርሱ ተሰበሰበ፥ ሕዝቡም እጅግ አለቀሱ። 2 ከዔላም ልጆች ወገን የነበረ፥ የይሒኤል ልጅ ሽካንያ ዕዝራን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለአምላካችን ታማኞች አልሆንም፥ የምድሪቱን ሕዝቦች እንግዶች ሴቶችን አግብተናል፥ አሁንም ግን በዚህ ነገር ለእስራኤል ተስፋ አለ። 3 ስለዚህ ከአምላካችን ጋር ቃል ኪዳን እናድርግ፥ ሚስቶችን ሁሉ ከእነርሱ የተወለዱትንም እንላካቸው፤ እንደ ጌታዬና በአምላካችን ትእዛዝ እንደሚንቀጠቀጡ ሕዝቦች ምክር፥ እንደ ሕጉም ይደረግ። 4 ተነሥ ይህም ነገር የአንተ ሥራ ነውና፥ እኛም ከአንተ ጋር እንሆናለን፤ በርታ፥ አድርገውም።” 5 ዕዝራም ተነሣ፤ አለቆቹን፥ ካህናቱን፥ ሌዋውያኑንና እስራኤልንም ሁሉ እንደዚህ ቃል እንዲያደርጉ አስማላቸው፥ እነርሱም ማሉ። የእንግዶች ሴቶችና ልጆቻቸው ተቀባይነት ማጣት 6 ዕዝራም ከእግዚአብሔር ቤት ፊት ተነሣ፥ ወደ ኤልያሺብ ልጅ ወደ ይሆሐናን ክፍል ገባ፤ ስለ ምርኮኞቹ አለመታመን አዝኖ ነበርና በዚያ ገብቶ እንጀራ አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። 7 ምርኮኞቹ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አዋጅ ነገሩ። 8 በሦስት ቀን ውስጥ ያልመጣ ሁሉ እንደ አለቆቹና እንደ ሽማግሌዎቹ ምክር ንብረቱ ሁሉ ይወረስ፥ እርሱም ከምርኮው ጉባኤ ይለይ፤ 9 በሦስት ቀን ውስጥ በዘጠነኛው ወር ከወሩም በሀያኛው ቀን የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሁሉ ስለዚህ ነገርና ስለ ታላቁ ዝናብ እየተንቀጠቀጡ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ባለው አደባባይ ተቀመጡ። 10 ካህኑ ዕዝራም ተነሣ እንዲህም አላቸው፦ “አልታመናችሁም፥ የእስራኤልን በደል ልታበዙ እንግዶች ሴቶችን አግብታችኋል። 11 ስለዚህ ለአባቶቻችሁ አምላክ ለጌታ ተናዘዙ፥ ፈቃዱንም አድርጉ፤ እራሳችሁንም ከምድሪቱ ሕዝቦችና ከእንግዶች ሴቶች ለዩ።” 12 ጉባኤውም ሁሉ በታላቅ ድምፅ እንዲህ ብለው መለሱ፦ “እንደ ተናገርኸን ማድረግ ይገባናል። 13 ነገር ግን ሕዝቡ ብዙ ነው፥ ጊዜውም የዝናብ ጊዜ ነው፥ በውጭ ልንቆም አንችልም፥ በዚህ ነገር እጅግ ተላልፈናልና ይህ ሥራ የአንድ ወይም የሁለት ቀን ሥራ አይደለም። 14 አለቆቻችንም ለጉባኤው ሁሉ ይቁሙ፥ ስለዚህም ነገር የአምላካችን የነደደው ቁጣ ከእኛ እንዲመለስ፥ እያንዳንዳቸው በከተሞቻችን ያሉ እንግዶቹን ሴቶች ያገቡት ሁሉ በተቀጠረው ጊዜ ይምጡ፥ ከእነርሱም ጋር የከተማ ሽማግሌዎችና ፈራጆች ይምጡ።” 15 የዐሣሄል ልጅ ዮናታንና የቲቅዋ ልጅ ያሕዝያ ብቻ ይህን ነገር ተቃወሙ፤ ምሹላምና ሌዋዊውም ሻብታይ ደገፏቸው። 16 ምርኮኞቹም እንዲህ አደረጉ፥ ካህኑ ዕዝራ፥ የአባቶችን መሪዎች መረጠ፤ በየአባቶቻቸው ቤቶች ተለዩ፥ ሁሉም በየስማቸው ተጻፉ፥ በአሥረኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ነገሩን ሊመረምሩ ተቀመጡ። 17 እስከ መጀመሪያው ወር፥ መጀመሪያው ቀን ድረስ እንግዶች ሴቶች ያገቡትን ሰዎች ሁሉ መርምረው ጨረሱ። 18 ከካህናቱ ልጆች እንግዶቹን ሴቶች ያገቡ ሰዎች ተገኙ፥ ከዮፃዳቅ ልጅ ከኢያሱ ልጆችና ከወንድሞቹ፥ ማዕሤያ፥ ኤሊዔዜር፥ ያሪብና ግዳልያ፤ 19 ሚስቶቻቸውን ለማሰናበት እጃቸውን ሰጡ፤ ስለ በደላቸውም ከመንጋው አንድ አውራ በግ ለበደል መሥዋዕት አቀረቡ። 20 ከኢሜርም ልጆች፥ ሐናኒና ዝባድያ፤ 21 ከሐሪም ልጆችም፦ ማዕሤያ፥ ኤልያ፥ ሽማዕያ፥ ይሒኤል፥ ዑዚያ፤ 22 ከፓሽሑር ልጆችም፦ ኤልዮዔናይ፥ ማዕሤያ፥ ዪሽማኤል፥ ናትናኤል፥ ዮዛባድ፥ ኤልዓሣ። 23 ከሌዋውያንም፦ ዮዛባድ፥ ሺምዒ፥ ቅሊጣ የሚባል ቄላያ፥ ፕታሕያ፥ ይሁዳ፥ ኤሊዔዜር። 24 ከመዘምራንም፦ ኤልያሺብ፥ ከበረኞችም፥ ሻሉም፥ ጤሌምና ኡሪ። 25 ከእስራኤልም ከፓርዖሽ ልጆች፦ ራምያ፥ ዪዚያ፥ ማልኪያ፥ ሚያሚን፥ ኤልዓዛር፥ ማልኪያና ብናያስ። 26 ከዔላም ልጆችም፦ ማታንያ፥ ዘካርያ፥ ይሒኤል፥ ዓብዲ፥ የሬሞትና ኤሊያ። 27 ከዛቱ ልጆችም፦ ዔልዮዔያይ፥ ኤልያሺብ፥ ማታንያ፥ ይሬሞት፥ ዛባድ፥ ዓዚዛ። 28 ከቤባይ ልጆችም፦ ይሆሐናን፥ ሐናንያ፥ ዘባይ፥ ዓትላይ። 29 ከባኒ ልጆችም፦ ምሹላም፥ ማሉክ፥ ዓዳያ፥ ያሹብ፥ ሽአል፥ ራሞት። 30 ከፓሐት ሞዓብ ልጆች፦ ዓድና፥ ክላል፥ ብናያስ፥ ማዕሤያ፥ ማታንያ፥ ብጻልኤል፥ ቢኑይና ምናሴ። 31 ከሓሪም ልጆችም፦ ኤሊዔዜር፥ ዪሺያ፥ ማልኪያ፥ ሽማዕያ፥ ስምዖን፥ 32 ብንያም፥ ማሉክና ሽማርያ። 33 ከሐሹም ልጆች፦ ማትናይ፥ ማታታ፥ ዛባድ፥ ኤሊፌሌጥ፥ ይሬማይ፥ ምናሴ፥ ሺምዒ። 34 ከባኒ ልጆችም፦ ማዕዳይ፥ ዓምራምና ኡኤል፥ 35 ብናያ፥ ቤድያ፥ ክሉሂ 36 ዋንያ፥ ምሬሞት፥ ኤልያሺብ፥ 37 ማታንያ፥ ማትናይና ያዐሦ፥ 38 ባኒ፥ ቢኑይ፥ ሺምዒ፥ 39 ሼሌምያ፥ ናታንና ዓዳያ 40 ማክናድባይ፥ ሻሻይ፥ ሻራይ፥ 41 ዓዛርኤል፥ ሼሌምያሁ፥ ሽማርያ፥ 42 ሻሉም፥ አማርያና ዮሴፍ። 43 ከንቦ ልጆችም፦ ይዒኤል፥ ማቲትያ፥ ዛባድ፥ ዝቢና፥ ያዳይ፥ ዮኤል፥ ብናያ። 44 እነዚህ ሁሉ እንግዶች ሚስቶችን አግብተው ነበር፤ ከእነዚህም አንዳንዶቹ ሚስቶች ልጆችን ወልደው ነበር። |