መሳፍንት 17:2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እናቱን፥ “አንድ ሺህ አንድ መቶ ሰቅል ብር ተሰርቆብሽ፥ የሰረቀውን ሰው ስትራገሚ ሰምቼሽ ነበር፤ ብሩ ከእኔ ዘንድ ይገኛል፤ የወሰድሁት እኔ ነኝ” አላት። ከዚያም እናቱ፥ “ልጄ፤ ጌታ ይባርክህ” አለችው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እናቱን፣ “አንድ ሺሕ አንድ መቶ ሰቅል ብር ተሰርቆብሽ፣ የሰረቀውን ሰው ስትራገሚ ሰምቼሽ ነበር፤ ብሩ ከእኔ ዘንድ ይገኛል፤ የወሰድሁት እኔ ነኝ” አላት። ከዚያም እናቱ፣ “ልጄ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ” አለችው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እርሱም አንድ ቀን እናቱን እንዲህ አላት፤ “አንድ ሰው አንድ ሺህ አንድ መቶ ጥሬ ብር በሰረቀሽ ጊዜ ያን የሰረቀሽን ሰው ስትረግሚው ሰምቼሽ ነበር፤ እነሆ ያ ብር በእኔ እጅ ነው፤ እርሱንም የወሰድኩ እኔ ነበርኩ።” እናቱም “ልጄ! እግዚአብሔር ይባርክህ!” አለችው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እናቱንም፥ “ከአንቺ ዘንድ የተሰረቀው፥ የረገምሽበትም፥ በጆሮዬም የተናገርሽበት አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር እነሆ፥ በእኔ ዘንድ አለ፤ እኔም ወስጄው ነበር” አላት። እናቱም፥ “ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ” አለችው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እናቱንም፦ ከአንቺ ዘንድ የተወሰደው፥ የረገምሽበትም፥ በጆሮዬም የተናገርሽበት አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር፥ እነሆ፥ በእኔ ዘንድ አለ፥ እኔም ወስጄዋለሁ አላት። እናቱም፦ ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ አለችው። |
ከእነርሱም ጋር ተከራከርሁ፥ ረገምኋቸውም፥ ከእነርሱም አያሌዎቹን መታሁ፥ ጠጉራቸውንም ነጨሁ፥ እንዲህም ብዬ በእግዚአብሔር አማልኋቸው፦ ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለእናንተና ለልጆቻችሁ አትውሰዱ።
አንድ ሺህ አንድ መቶውን ሰቅል ብር በመለሰላት ጊዜ፥ እናቱ “ብሬን የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት ለማበጀት ስለ ልጄን ለጌታ እቀድሰዋለሁ፤ አሁንም ለአንተው መልሼ እሰጥሃለሁ” አለችው።
የጌታ መልአክ፦ ሜሮዝን እርገሙ፥ ጌታን በኃያላን መካከል ለመርዳት፥ ጌታን ለመርዳት አልመጡምና የተቀመጡባትን ሰዎች ፈጽማችሁ እርገሙ አለ።
ቦዔዝም አላት፦ “ልጄ ሆይ፥ በጌታ የተባረክሽ ሁኚ፥ ባለ ጠጋ ይሁን ወይም ድሀ፥ ወጣቶችን መርጠሽ መሄድ አልፈለግሽምና ከፊተኛው ይልቅ አሁን ባደረግሽው ታማኝነትን አድርገሻል።
ሳኦል፥ “ዛሬ ጠላቶቼን ከመበቀሌ በፊት፥ እስከ ማታ ድረስ እህል የሚበላ ሰው የተረገመ ይሁን” ብሎ ሕዝቡን አስምሎ ስለ ነበር፥ በዚያች ዕለት የእስራኤል ሰዎች ተጨንቀው ዋሉ፤ ስለዚህ ከሕዝቡ አንድም እህል የቀመሰ አልነበረም።
ከሕዝቡም አንድ ሰው፥ “አባትህ ሕዝቡን፥ ‘ዛሬ እህል የሚቀምስ ማናቸውም ሰው የተረገመ ይሁን!’ በማለት በጽኑ መሓላ አስጠንቅቆናል” አለው። ሰው ሁሉ ተዳክሞ ነበር።
አሁንም ንጉሥ ጌታዬ የባርያውን ቃል ያድምጥ፤ ጌታ በእኔ ላይ አነሣሥቶህ እንደሆነ፥ መሥዋዕት ይቀበል፤ ነገር ግን ይህን ያደረጉት ሰዎች ከሆኑ፥ በጌታ ፊት የተረገሙ ይሁኑ፥ ‘ሂድ ሌሎችን አማልክት አምልክ’ ብለው በጌታ ርስት ድርሻ እንዳይኖረኝ ዛሬ አሳደውኛልና።