Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መሳፍንት 5 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የዲቦራና የባራቅ መዝሙር

1 በዚያም ቀን ዲቦራና የአቢኒኤም ልጅ ባራቅ እንዲህ ብለው ተቀኙ፦

2 በእስራኤል ውስጥ መሪዎች ስለ መሩ፥ ሕዝቡም ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ስለ ሰጡ፥ ጌታን አመስግኑ።

3 ነገሥታት ሆይ፥ ስሙ፥ መኳንንት ሆይ፥ አድምጡ፥ እኔ ለጌታ እቀኛለሁ፥ ለእስራኤል አምላክ ለጌታ እዘምራለሁ።

4 አቤቱ፥ ከሴይር በወጣህ ጊዜ፥ ከኤዶምያስም ሜዳ በተራመድህ ጊዜ፥ ምድሪቱ ተናወጠች፥ ሰማያቱም አንጠበጠቡ፥ ደመናትም ደግሞ ውኃን አንጠበጠቡ።

5 ከእስራኤል አምላክ ከጌታ ፊት፥ በሲናው ጌታ ፊት ተራሮች ቀለጡ።

6 በዓናት ልጅ በሻምጋር ዘመን፥ በያዔል ዘመን መንገዶች ተቋረጡ፥ መንገደኞች በስርጥ መንገድ ይሄዱ ነበር።

7 አንቺ፥ ዲቦራ፥ እስክትነሽ ድረስ፥ ለእስራኤልም እናት ሆነሽ እስክትነሽ ድረስ፥ ኃያላን በእስራኤል ዘንድ አነሱ፥ አለቁም።

8 አዲሶች አማልክትን መረጡ፥ በዚያ ጊዜ ሰልፍ በበሮች ሆነ፥ በአርባ ሺህ በእስራኤል ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታየም።

9 ልቤ ወደ እስራኤል አለቆች ነው፥ በሕዝቡ መካከል ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ወደ ሰጡት፥ ጌታን አመስግኑ።

10 በነጫጭ አህዮች ላይ የምትጫኑ፥ በወላንሳ ላይ የምትቀመጡ፥ በመንገድም የምትሄዱ፥ ተናገሩ።

11 በማጠጫው መካከል ካሉት ከቀስተኞች ጩኸት ርቀው፥ በዚያ የጌታን ጽድቅ፥ በእስራኤል ላይ የግዛቱን ጽድቅ ይጫወታሉ፥ ከዚያም በኋላ የጌታ ሕዝብ ወደ በሮች ወረዱ።

12 ንቂ፥ ንቂ፥ ዲቦራ ሆይ፥ ንቂ፥ ንቂ፥ ቅኔውን ተቀኚ፥ ባራቅ ሆይ፥ ተነሣ፥ የአቢኒኤም ልጅ ሆይ፥ ምርኮህን ማርክ።

13 በዚያ ጊዜ የቀሩት ወደ ኃያላኑና ወደ ሕዝቡ ወረዱ፥ ጌታም ስለ እኔ በኃያላን ላይ ወረደ።

14 በአማሌቅ ዘንድ ሥር የነበራቸው እነርሱ ከኤፍሬም፥ ብንያም ሆይ፥ በሕዝብህ መካከል ከአንተ በኋላ ወረዱ፥ አለቆች ከማኪር፥ የንጉሥንም ዘንግ የሚይዙ ከዛብሎን ወረዱ።

15 የይሳኮርም አለቆች ከዲቦራ ጋር ነበሩ፥ ይሳኮርም እንደ ባራቅ ነበረ፥ ከእግሩ በኋላ ወደ ሸለቆው ቸኰሉ፥ በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ብዙ የልብ ማመንታት ነበረ።

16 መንጎች ሲያፍዋጩ ለመስማት በበጎች ጉረኖ መካከል ለምን ተቀመጥህ? በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ታላቅ የልብ ምርምር ነበረ።

17 ገለዓድ በዮርዳኖስ ማዶ ተቀመጠ፥ ዳንም ለምን በመርከብ ውስጥ ቀረ? አሴርም በባሕሩ ዳር ተቀመጠ፥ በወንዞቹም ዳርቻ ዐረፈ።

18 ዛብሎን ነፍሱን ወደ ሞት ያሳለፈ ሕዝብ ነው፥ ንፍታሌምም በአገሩ ኮረብታ ላይ ነው።

19 ነገሥታት መጡ፥ ተዋጉም፥ በዚያ ጊዜ በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክ የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፥ የብር ዘረፋም አልወሰዱም።

20 ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፥ በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ።

21 ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥ የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው። ነፍሴ ሆይ፥ በኃይል እርገጪ።

22 ከኃያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ።

23 የጌታ መልአክ፦ ሜሮዝን እርገሙ፥ ጌታን በኃያላን መካከል ለመርዳት፥ ጌታን ለመርዳት አልመጡምና የተቀመጡባትን ሰዎች ፈጽማችሁ እርገሙ አለ።

24 የቄናዊው የሔቤር ሚስት ያዔል ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፥ በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን።

25 ውኃ ለመነ፥ ወተትም ሰጠችው፥ በተከበረ ጽዋ እርጎ አቀረበችለት።

26 እጅዋን ወደ ካስማ፥ ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፥ በመዶሻውም ሲሣራን መታች፥ ራሱንም ቸነከረች፥ ጆሮግንዱንም በሳች፥ ጎዳችውም።

27 በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ ተኛ፥ በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ በተደፋበት ስፍራ በዚያ ወድቆ ሞተ።

28 ከመስኮት ሆና ተመለከተች፥ የሲሣራ እናት በሰቅሰቅ ዘልቃ፦ “ስለምን ለመምጣት ሠረገላው ዘገየ? ስለ ምንስ የሠረገላው መንኰራኵር ቈየ?” ብላ ጮኸች።

29 ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፥ እርሷ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች፦

30 “ምርኮ አግኝተው የለምን? ተካፍለውስ የለምን? ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ቈነጃጅት፥ ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ያለው ልብስ፥ በአንገትጌ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጉርጉር ልብስ።”

31 አቤቱ፥ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፥ ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፥ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos