Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ሳሙኤል 26 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ዳዊት ለሁለተኛ ጊዜ ሳኦልን ማትረፉ

1 የዚፍ ሰዎችም ወደ ጊብዓ ወደ ሳኦል መጥተው፦ “እነሆ፥ ዳዊት በየሴሞን ፊት ለፊት ባለው በሐኪላ ኮረብታ ላይ ተሸሽጓል” አሉት።

2 ስለዚህ ሳኦል ተነሣ፤ ዳዊትን ፍለጋ ወደ ዚፍ ምድረ በዳ ከእስራኤል የተመረጡ ሦስት ሺህ ሰዎችን ይዞ ወረደ።

3 ሳኦልም በየሴሞን ትይዩ በሚገኘው በሐኪላ ኰረብታ ላይ በመንገድ ዳር ሰፈረ፤ ዳዊት ግን በምድረ በዳ ነበር። ዳዊትም ሳኦል እዚያ ድረስ እንደ ተከተለው ባወቀ ጊዜ፥

4 ሰላዮች ልኮ በትክክል ሳኦል መምጣቱን አረጋገጠ።

5 ዳዊትም ተነሥቶ ሳኦል ወደ ሰፈረበት ቦታ ሄደ፤ ሳኦልና የሠራዊቱ አለቃ፥ የኔር ልጅ አበኔር የተኙበትን ስፍራ አየ። ሠራዊቱ በዙሪያው ሰፍሮ፥ ሳኦል በሰፈሩ መካከል ተኝቶ ነበር።

6 ዳዊትም ሒታዊውን አቢሜሌክንና የጸሩያን ልጅ የኢዮአብን ወንድም አቢሳን፥ “ወደ ሳኦል ሰፈር አብሮኝ የሚወርድ ማነው?” ሲል ጠየቃቸው። አቢሳም፥ “እኔ አብሬህ እወርዳለሁ” አለ።

7 ስለዚህም በዚያው ምሽት ዳዊትና አቢሳን ወደ ሳኦል ሰፈር ገቡ፤ ሳኦልንም በሰፈሩ መካከል ተኝቶ አገኙት፤ ጦሩም በራስጌው በኩል መሬት ላይ ተተክሎ ነበር፤ አበኔርና ወታደሮቹም በዙሪያው ተኝተዋል፤፥

8 አቢሳም ዳዊትን፥ “ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ ላይ ጥሎታል፤ አሁንም እኔ አንድ ጊዜ በጦር ወግቼ ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ መድገምም አያስፈልገኝም” አለው።

9 ዳዊት ግን አቢሳን እንዲህ አለው፤ “አትግደለው! ጌታ በቀባው ላይ እጁን አንሥቶ ከበደል ነጻ የሚሆን ማን ነው?

10 ሕያው ጌታ አለ፥ ጌታ ራሱ ይቀሥፈዋል፤ ወይም የመሞቻው ቀን ይመጣል፤ ወይም በጦርነት ይሞታል፤ ይጠፋልም።

11 ጌታ በቀባው ላይ እጄን ከማንሣት ጌታ ይጠብቀኝ! ነገር ግን በራስጌው አጠገብ ያለውን ጦርና የውሃ መያዣውን ያዝና እንሂድ።”

12 ስለዚህ ዳዊት በሳኦል ራስጌ አጠገብ የነበረውን ጦርና የውሃውን መያዣ ወሰደ፤ ከዚያም ሄዱ፤ ይህን ያየም ሆነ ያወቀ ወይም የነቃ ማንም አልነበረም። ከእግዚአብሔር ዘንድ ከባድ እንቅልፍ ስለ ወደቀባቸው ሁሉም ተኝተው ነበርና።

13 ከዚህ በኋላ ዳዊት ወደ ማዶ ተሻግሮ በኰረብታው ጫፍ ላይ ራቅ ብሎ ቆመ፤ በመካከላቸውም ሰፊ ርቀት ነበር።

14 ዳዊት ሠራዊቱንና የኔርን ልጅ አቤኔርን፥ “አቤኔር ሆይ፥ አትመልስልኝምን?” ሲል ተጣራ። አቤኔርም፥ “በንጉሡ ላይ የምትጮኽ አንተ ማነህ?” በማለት መለሰ።

15 ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “አንተ ብርቱ ሰው አይደለህምን? በእስራኤልስ ዘንድ አንተን የሚመስል ማን ነው? እነሆ፤ አንድ ሰው ንጉሡን ጌታህን ለመግደል መጥቶ ነበር፤ ታዲያ አንተ ንጉሥ ጌታህን ያልጠበቅኸው ስለ ምንድነው?

16 ይህ ያደረግኸው ነገር መልካም አይደለም፤ በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ፥ አንተና ሰዎችህ ሞት ይገባችኋል፤ ጌታ የቀባውን ጌታችሁን አልጠበቃችሁም። እስቲ ተመልከት፤ በራስጌው የነበሩት የንጉሡ ጦርና የውሃ መያዣ የት አሉ?”

17 ሳኦል የዳዊትን ድምፅ ለይቶ ስላወቀ፥ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ በእርግጥ የአንተ ድምፅ ነውን?” አለው። ዳዊትም፥ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ አዎን ድምፄ ነው” ሲል መለሰ፤

18 በመቀጠልም፥ “ጌታዬ አገልጋዩን የሚያሳድደው ስለ ምንድነው? ምን አደረግሁ? ምን በደልስ ፈጸምሁ?

19 አሁንም ንጉሥ ጌታዬ የባርያውን ቃል ያድምጥ፤ ጌታ በእኔ ላይ አነሣሥቶህ እንደሆነ፥ መሥዋዕት ይቀበል፤ ነገር ግን ይህን ያደረጉት ሰዎች ከሆኑ፥ በጌታ ፊት የተረገሙ ይሁኑ፥ ‘ሂድ ሌሎችን አማልክት አምልክ’ ብለው በጌታ ርስት ድርሻ እንዳይኖረኝ ዛሬ አሳደውኛልና።

20 አሁንስ ከጌታ ርቄ በባዕድ አገር እንድገደል አታድርግ፤ አሁንም በተራራው ላይ ቆቅን እንደሚሻ ሰው ይህን ያህል የእስራኤል ንጉሥ እኔን ስለምን ያሳድዳል?”

21 ሳኦልም፥ “ልጄ ዳዊት ሆይ! በእርግጥ ተሳስቻለሁ፤ ተመለስ፤ ዛሬ ነፍሴ በፊትህ ስለከበረች ከእንግዲህ ወዲያ አልጐዳህም፤ ይሄው፥ የሞኝ ሥራ ሠራሁ፤ አብዝቼም ተሳሳትኩ” አለ።

22 ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ንጉሥ ሆይ! እነሆ ጦርህ፤ ከወጣቶችህ አንዱ መጥቶ ይውሰዳት።

23 ጌታ ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ጽድቁና እንደ ታማኝነቱ ይክፈለው። እኔ ግን ዛሬ አንተን ጌታ በእጄ አሳልፎ ሰጥቶኝ ሳለ ጌታ በቀባው ላይ እጄን አላነሣሁም።

24 እነሆ፤ ዛሬ ሕይወትህ በፊቴ እንደ ከበረች ሁሉ፥ የእኔም ሕይወት በጌታ ዘንድ የከበረች ትሁን፤ ከመከራም ሁሉ ያድነኝ።”

25 ከዚያም ሳኦል ዳዊትን፥ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ የተባረክህ ሁን፤ ብዙ ነገር ታደርጋለህ፤ በእርግጥም ይከናወንልሃል” አለው። ስለዚህም ዳዊት ወደሚሄድበት ሄደ፤ ሳኦልም ወደ ስፍራው ተመለሰ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos