1 ቆሮንቶስ 8:4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እንግዲህ ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ ስለ መብላት፥ ጣዖት በዓለም ከንቱ እንደ ሆነና ከአንዱ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እንግዲህ፣ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ስለ መብላት፣ በዚህ ዓለም ጣዖት ከንቱ እንደ ሆነና ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ስለዚህ ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ ስለ መብላት የሆነ እንደ ሆነ ጣዖት ሕይወት የሌለው እንደ ሆነና ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ለጣዖታት የተሠዋውን ስለመብላት ግን ጣዖት ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደሆነ፥ ከአንድ እግዚአብሔርም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እንግዲህ ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ ስለ መብላት፥ ጣዖት ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደ ሆነ ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። |
“አቤቱ የሠራዊት ጌታ፥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አንተ ብቻህን የምድር መንግሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል።
ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ ጌታ እኔ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ማን ነበረ?
ጌታ እንዲህ ይላል፦ የግብጽ ድካምና የኢትዮጵያ ንግድ ቁመተ ረጅሞችም የሳባ ሰዎች ወደ አንተ ያልፋሉ፤ ለአንተም ይሆናሉ እጆቻቸውም ታስረው ይከተሉሃል፤ በፊትህም ያልፋሉ፥ ለአንተም እየሰገዱ፦ በእውነት እግዚአብሔር በአንተ አለ፥ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም ብለው ይለምኑሃል።
ጌታ ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤ እርሱም ሕያው አምላክና የዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ ከቁጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ አሕዛብም መዓቱን መቋቋም አይችሉም።
ሰው ሁሉ ቂላ ቂልና እውቀት የሌለው ሆኖአል፥ አንጥረኛም ሁሉ ከቀረጸው ምስል የተነሣ አፍሮአል፤ ቀልጦ የተሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስትንፋስም የላቸውምና።
እንዲህም አሉ “እናንተ ሰዎች! ይህን ስለምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፤ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእርነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ትመለሱ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን።
ይህም ጳውሎስ ‘በእጅ የተሠሩቱ አማልክት አይደሉም፤’ ብሎ፥ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብን እንደ አስረዳና እንደ አሳተ አይታችኋል፤ ሰምታችሁማል።
አንተ ዕውቀት ያለህ በጣዖት ቤት በማዕድ ስትቀመጥ አንድ ሰው ቢያይህ፥ ደካማ ሰው ቢሆን ለጣዖት የተሠዋውን ለመብላት ሕሊናው አይደፋፈርምን?
‘ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ታላቅነትህን የጸናችውንም እጅህን ለእኔ ለአገልጋይህ ማሳየት ጀምረሃል፥ በሰማይም ሆነ በምድርም እነዚህ ሥራዎችና ኃያል ተግባራት እንደ አንተ ማድረግ የሚችል አምላክ ማን ነው?
“እኔ ራሴ እርሱ እንደሆንሁ እዩ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ እኔ እገድላለሁ፤ በሕይወትም አኖራለሁ፤ እኔ አቆስላለሁ፤ እፈውሳለሁም፤ ከእጄም የሚያስጥል ማንም የለም።
እርሱ ብቻ አዳኛችን ለሆነው አምላክ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ክብር፥ ግርማ፥ ኃይልና ሥልጣን ከዘመናት ሁሉ በፊት፥ አሁንም እስከ ዘለዓለምም ድረስ ይሁን፤ አሜን።