ዘኍል 21:7 - መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው፦ በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ስለ ተናገርን በድለናል፤ እባቦችን ከእኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን አሉት። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥቶ፣ “በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ በመናገራችን በድለናል፤ እባቦቹን ከእኛ እንዲያርቅልን ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን” አለ፤ ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው እንዲህ አሉት፦ “በጌታና በአንተ ላይ ስለ ተናገርን ኃጢአት ሠርተናል፤ እባቦቹን ከእኛ እንዲያርቅልን ወደ ጌታ ጸልይልን።” ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው፥ “በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ክፉ ቃል በመናገራችን በድለናል፤ አሁንም እነዚህ ተናዳፊ እባቦች ከእኛ እንዲወገዱ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን” አሉት፤ ሙሴም ለሕዝቡ ጸለየ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው፥ “በእግዚአብሔርና በአንተ ስለ ተናገርን በድለናል፤ እባቦችን ከእኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን” አሉት። ሙሴም ስለ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። |
አሁንም የሰውዩውን ሚስት መልስ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፤ ትድናለህም። ባትመልሳት ግን አንተ እንድትሞት ለአንተ የሆነውም ሁሉ እንዲሞት በእርግጥ እወቅ።
ንጉሡም የእግዚአብሔርን ሰው “አሁን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ፊት ለምን፤ እጄም ወደ እኔ ትመለስ ዘንድ ስለ እኔ ጸልይ፤” አለው። የእግዚአብሔርም ሰው እግዚአብሔርን ለመነ፤ የንጉሡም እጅ ወደ እርሱ ተመለሰች፤ እንደ ቀድሞም ሆነች።
ኢዮብም ስለ ወዳጆቹ በጸለየ ጊዜ እግዚአብሔርም ምርኮውን መለሰለት፥ እግዚአብሔር ቀድሞ በነበረው ፋንታ ሁለት እጥፍ አድርጎ ለኢዮብ ሰጠው።
አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፥ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፥ ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፥ እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ፥ እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና።
አሁን እንግዲህ በዚህ ጊዜ ብቻ ኃጢአቴን ይቅር በሉኝ፤ ይህንም ሞት ብቻ ከእኔ ያነሣልኝ ዘንድ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለምኑ አላቸው፤”
ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፥ አለም፦ አቤቱ፥ ቁጣህ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብፅ ምድር ባወጣኸው በሕዝብህ ላይ ስለ ምን ተቃጠለ?
በነጋውም ሙሴ ለሕዝቡ፦ እናንተ ታላቅ ኃጢአት ሠርታችኋል፤ አሁንም ወደ እግዚአብሔር እወጣለሁ፤ ምናልባት ኃጢአታችሁን አስተሰርይላችኋለሁ አላቸው።
ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ “ጓጕንቸሮቹን ከእኔ ከሕዝቤም እንዲያርቅ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ፤ ለእግዚአብሔርም ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እለቅቃለሁ፤” አላቸው።
ንጉሡም ሴዴቅያስ፦ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ስለ እኛ ጸልይ ብሎ የሰሌምያን ልጅ ዮካልንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ ላከ።
እርሱም፦ በድያለሁ፥ አሁን ግን በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊትና በእስራኤል ፊት፥ እባክህ፥ አክብረኝ፥ ለአምላክህም ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተምለስ አለው።