ዘኍል 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበከነዓናውያን ላይ የተገኘ ድል 1 መኖሪያው ኔጌብ የነበረ የከነዓናውያን ንጉሥ ዐራድ እስራኤላውያን በአታሪም በኩል መምጣታቸውን በሰማ ጊዜ በእነርሱ ላይ አደጋ ጥሎ ጥቂቶቹን ማረከ። 2 በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን “ይህን ሕዝብ ድል እንድንነሣው ብትረዳን፥ እነርሱንም ሆኑ ከተሞቻቸውን ዳግመኛ እንዳያንሰራሩ አድርገን በፍጹም እንደመስሳቸዋለን” በማለት ለእግዚአብሔር ተሳሉ። 3 እግዚአብሔርም ልመናቸውን ሰምቶ ስለ ረዳቸው ከነዓናውያንን ድል ነሥተው ያዙ፤ ስለዚህ እስራኤላውያን እነርሱንና ከተሞቻቸውን ፈጽመው ደመሰሱ፤ ፈጽሞ የተደመሰሱ መሆናቸውንም ለማመልከት ያን ስፍራ “ሖርማ” ብለው ሰየሙት። ከነሐስ የተሠራው እባብ 4 እስራኤላውያን በኤዶም ግዛት ዙሪያ ለመሄድ አስበው ከሖር ተራራ ተነሥተው ወደ ቀይ ባሕር በሚወስደው መንገድ ተጓዙ፤ ነገር ግን በመንገድ ሳሉ የሕዝቡ ትዕግሥት አለቀ፤ 5 በእግዚአብሔርና በሙሴም ላይ ክፉ ቃል በመናገር እንዲህ ሲሉ አጒረመረሙ፤ “ምግብና ውሃ በሌለበት በዚህ በረሓ እንሞት ዘንድ ከግብጽ ምድር ለምን አወጣችሁን? ይህን አስከፊ ምግብ ሰውነታችን ተጸይፎታል!” 6 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር መርዘኛ እባብ ወደ ሕዝቡ ስለ ላከ ብዙ እስራኤላውያን ተነድፈው ሞቱ። 7 ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው፥ “በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ክፉ ቃል በመናገራችን በድለናል፤ አሁንም እነዚህ ተናዳፊ እባቦች ከእኛ እንዲወገዱ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን” አሉት፤ ሙሴም ለሕዝቡ ጸለየ። 8 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ሙሴን “አንድ የነሐስ እባብ ሠርተህ በረዥም ትክል እንጨት ላይ ስቀለው፤ በእባብ የተነከሰ ሁሉ እርሱን በሚያይበት ጊዜ ይድናል” አለው። 9 ሙሴም የነሐስ እባብ ሠርቶ በእንጨት ላይ ሰቀለው፤ በእባብ የተነከሰም ሁሉ ወደ ነሐሱ እባብ ቀና ብሎ ሲመለከት ዳነ። ከሖር ተራራ ወደ ሞአባውያን ሸለቆ የተደረገ ጒዞ 10 እስራኤላውያን ጒዞአቸውን ቀጥለው በኦቦት ሰፈሩ፤ 11 ያንንም ስፍራ ከለቀቁ በኋላ ከሞአባውያን ግዛት በስተ ምሥራቅ ባለው በረሓ ውስጥ በተለይ “ዐባሪም” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ሰፈሩ። 12 ከዚያም አልፈው በዘሬድ ሸለቆ ሰፈሩ። 13 ከዚያም ተጒዘው እስከ አሞራውያን ግዛት በሚዘልቀው ምድረ በዳ ከአርኖን ወንዝ ማዶ በሚገኘው ቦታ ሰፈሩ፤ የአርኖን ወንዝ በሞአባውያንና በዐሞራውያን ግዛት ወሰን ላይ የሚገኝ ነው። 14 ከዚህም የተነሣ በእግዚአብሔር መሪነት ስለ ተደረገው ጦርነት በሚናገር የታሪክ መጽሐፍ እንዲህ ተብሎአል፦ “በሱፋ ክልልና በሸለቆዎች ውስጥ የሚገኘው ዋሄብ፥ የአርኖን ወንዝ፥ 15 እስከ ዔር ከተማና እስከ ሞአብ ወሰን የሚዘልቁት ሸለቆዎች ሸንተረር” 16 ከዚያም ተነሥተው “የውሃ ጒድጓዶች” ወደ ተባለው ስፍራ ሄዱ፤ በእዚያም እግዚአብሔር ሙሴን “ሕዝቡን በአንድነት ሰብስባቸውና ውሃ እሰጣቸዋለሁ” አለው። 17 በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን ይህን መዝሙር ዘመሩ “ጒድጓድ ሆይ፥ ውሃ አፍልቅ፤ ለእርሱም ዘምሩለት 18 የውሃ ጒድጓዱን የቈፈሩት፥ መሳፍንትና የሕዝብ አለቆች ናቸው፤ እነርሱም የውሃ ጒድጓዱን የቈፈሩት በበትረ መንግሥታቸውና በከዘራቸው ነው።” ከዚያም ምድረ በዳ ተነሥተው ወደ ማታና ተጓዙ፤ 19 ከማታናም ወደ ናሕሊኤል፥ ከናሕሊኤልም ወደ ባሞት ዘለቁ፤ 20 ከባሞትም ተነሥተው በሞአባውያን ግዛት ውስጥ ወዳለው ሸለቆ ተጓዙ፤ ይህም ሸለቆ የሚገኘው ከፒስጋ ተራራ ግርጌ በበረሓው ትይዩ ነው። የንጉሥ ሲሖንና የንጉሥ ዖግ ድል መመታት ( ዘዳ. 2፥26—3፥11 ) 21 ከዚህ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ወደ አሞራውያን ንጉሥ ሲሖን እንዲህ ብለው የሚነግሩትን መልእክተኞች ላኩ፤ 22 “በምድርህ አልፈን እንድንሄድ ፍቀድልን፤ እኛና ከብቶቻችን ከመንገዱ አንወጣም፤ ወደ እርሻዎችህም ሆነ ወደ ወይን ተክሎችህ አንገባም፤ ከውሃ ጒድጓዶችህም ውሃ አንጠጣም፤ ከግዛትህ እስክንወጣ ድረስ ዋናውን መንገድ አንለቅም።” 23 ሲሖን ግን የእስራኤል ሕዝብ በግዛቱ አልፈው እንዲሄዱ አልፈቀደላቸውም፤ እንዲያውም ሠራዊቱን ሁሉ ሰብስቦ በበረሓ ውስጥ ወዳለችው ወደ ያሀጽ በመሄድ በእስራኤላውያን ላይ ጦርነት አደረገ። 24 እስራኤላውያን ግን ድል ነሡአቸው፤ ከአርኖን ወንዝ አንሥቶ በስተሰሜን እስከ ዐሞናውያን ወሰን ማለትም እስከ ያቦቅ ወንዝ ድረስ የሚገኘውን ግዛት ያዙ፤ ይሁን እንጂ የዐሞናውያን ወሰን በብርቱ የተጠበቀ በመሆኑ ወደዚያ አልገቡም። 25 በዚህ ዐይነት የእስራኤል ሕዝብ የአሞራውያንን ከተሞች ሐሴቦንንና በዙሪያ ያሉትን ታናናሽ ከተሞች ጭምር ይዘው በዚያ ተቀመጡ፤ 26 ሐሴቦን የአሞራውያን ንጉሥ ሲሖን መናገሻ ከተማ ነበረች፤ እርሱም ከሞአብ የቀድሞ ንጉሥ ጋር ተዋግቶ እስከ አርኖን ወንዝ ያለውን ምድር ሁሉ ወስዶበት ነበር። 27 ከዚህም የተነሣ ባለቅኔዎች እንኳ እንዲህ እያሉ ይቀኙ ነበር፦ “ወደ ሐሴቦን ኑ! ይህች ከተማ ትገንባ! የሲሖን ከተማ ትመሥረት፤ 28 ከሐሴቦን እሳት ወጣ፤ ነበልባልም ከሲሖን ከተማ፥ የሞአብን ዔር አጠፋ የአርኖንንም ከፍተኛ ቦታዎች ደመሰሰ። 29 ሞአብ ሆይ! ወዮልሽ! እናንተ የከሞሽ ሰዎች ሆይ! ትደመሰሳላችሁ፤ ወንዶች ልጆቹን ስደተኞች እንዲሆኑ አደረጋቸው፤ ሴቶች ልጆቹንም ንጉሥ ሲሖን እንዲማረኩ አደረገ። 30 ስለዚህ ዘሮቻቸው ተደመሰሱ ከሐሴቦን እስከ ዲቦን፥ እሳቱ እስከ ሜዴባ እስኪስፋፋ ድረስ አጠፋናቸው።” 31 ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ በአሞራውያን ግዛት ውስጥ ተቀመጡ፤ 32 ሙሴም ያዕዜርን የሚሰልሉ ሰዎች ላከ፤ እስራኤላውያንም ከተማይቱንና በዙሪያዋ ያሉትን ታናናሽ ከተሞች ያዙ፤ በዚያም ይኖሩ የነበሩትን አሞራውያን አባረሩ። ንጉሥ ዖግ ተሸነፈ 33 ከዚያም በኋላ እስራኤላውያን ተመልሰው ወደ ባሳን የሚወስደውን መንገድ ተከትለው ሄዱ፤ የባሳን ንጉሥ ዖግ በኤድረዒ ከእነርሱ ጋር ጦርነት ለመግጠም ከመላ ሠራዊቱ ጋር ወጣ። 34 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ይህን ሰው አትፍራው፤ በእርሱና በሕዝቡ በምድሪቱም ላይ ድል እንድትጐናጸፍ አደርግሃለሁ፤ በሐሴቦን ሆኖ ይገዛ በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሲሖን ላይ ያደረግኸውን ሁሉ በዚህም ላይ አድርግበት።” 35 ስለዚህ እስራኤላውያን ዖግን፥ ልጆቹን፥ ሕዝቡን ሁሉ አንድም ሳያስቀሩ ፈጅተው ምድሩን ወረሱ። |