ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጥበብ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ከበጎነት ጋር አለመውለድ ፍጹም ሥራ ነው፤ በእግአብሔር ዘንድ፥ በሰውም ዘንድ የታወቀች ስለ ሆነች ስም አጠራሯ ሕይወት ነውና። 2 በዚህ ዓለም ሳለችም ያከብሯታል፤ ካለፈችም በኋላ ፈጽመው ይወድዷታል፤ በዚህም ዓለም የገድል ድልን እግኝታ፥ የማያልፍ አክሊልንም ተቀዳጅታ ትኖራለች። 3 የክፉዎች ሰዎች ልጆች ብዛት አይረባም፤ የከንቱ ተክልም ሥሯ አይታወቅም፤ ጽኑ አኗኗርም አታደርግም። 4 ለጊዜውም በቅርንጫፎችዋ ላይ ቅጠል ቢወጣ ሳያድግ ነፋስ ያነዋውጠዋል፤ በነፋሱም ኀይል ይነቀላል። 5 ቅርንጫፎችዋም ሳያድጉ ይሰበራሉ፥ ፍሬያቸውም ለመብል የማይሆን ከንቱ ጨርቋ ነው፤ ጊዜው አይደለምና፥ ለመብላትም አይገባምና። 6 ከክፉዎች ሰዎች መኝታ የሚወለዱ ልጆችም በተመረመሩ ጊዜ ለእናትና አባታቸው ክፋት ምስክሮች ናቸው። 7 ጻድቅ ሰው ግን ለመሞት በደረሰ ጊዜ በዕረፍት ይኖራል። 8 የሽምግልና ክብር በዕድሜ ብዛት አይደለም፤ በዓመታትም ቍጥር የሚቈጠር አይደለም። 9 ሽበትስ የሰው ዕውቀቱ ነው፤ የሽምግልናም አክሊሏ ያለ ነውር መኖር ነው። 10 እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሰው በእርሱ ዘንድ የሚወደድ ይሆናል፤ በኀጢአተኞችም መካከል ሲኖር ይለያል። 11 ክፋትም ዕውቀቱን ሳትለውጥበት፥ ይህም ባይሆን ሐሰት ሰውነቱን ሳታስትበት ተነጥቆ ይሄዳል። 12 የክፋት ቅንዐት በጎ ሥራዎችን ያጠፋልና፥ የፈቃድ ነዘህላልነትም የዋህ ልቡናን ይለውጣልና። 13 በጥቂት ዘመንም ቢሞት ረዥም ዓመታትን ጨርሷል። 14 ነፍሱ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝታዋለችና፤ ስለዚህም ከክፉዎች መካከል ተለይቶ በችኮላ ሄደ። 15 ልዩ የሆኑ ሰዎች ግን ይህን አይተው ልብ አላደረጉትም፤ የዚህንም ትርጓሜ በልባቸው አላሳደሩትም። የእግዚአብሔር ጸጋው ለጻድቃኑ ነውና የይቅርታው ጕብኝትም ለመረጣቸው ሰዎች ነውና። የቅዱሳን ድል አድራጊነትና የኃጥኣን ፍርድ 16 ጻድቅ ሰው ከሞተ በኋላ በሕይወት ባሉ ክፉዎች ላይ ይፈርዳል። ጐልማሳ ሰውም ፈጥኖ በሚሞትበት ጊዜ የዐመፃ ሽምግልና ዕድሜአቸው በበዛ በክፉዎች ሰዎች ላይ ይፈርዳል። 17 ጠቢብ የሆነ የጻድቁን ሞት አይተው እግዚአብሔር ስለ እርሱ ምን እንደ መከረ፥ ወደ እርሱም ለምን እንደ ሰበሰበው አያስተውሉምና። 18 እርሱንም አይተው በእርሱ ይጠቃቀሳሉ፤ እግዚአብሔር ግን በእነርሱ ይሥቃል። 19 ከዚህም በኋላ ለጐስቋላ ሞት ይሆናሉ፤ ለዘለዓለምም ሙታን ለሚሰደቡበት ስድብ ይሆናሉ። ይቈርጣቸዋልና፥ ይሰነጥቃቸዋልምና፥ ቃልም ሳይኖራቸው በፊታቸው የወደቁ ሆነው ይገኛሉ። ከመሠረታቸውም ያነዋውጣቸዋል፤ ለዘለዓለሙ እንደ ተፈታች ምድር ይሆናሉ፥ የተጨነቁም ይሆናሉ፤ መታሰቢያቸውም ይጠፋል። 20 በፍርሃትም ሆነው በኀጢኣታቸው ለመወቀስ ይቀርባሉ፤ ኀጢኣታቸውም በፊታቸው ተገልጦ ይዘልፋቸዋል። |