መዝሙር 76 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ ስለ ኤዶታም የአሳፍ መዝሙር። 1 በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ ቃሌም ወደ እግዚአብሔር ነው፥ እርሱም አደመጠኝ። 2 በመከራዬ ቀን እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤ እጆቼም በሌሊት በፊቱ ናቸው፥ ጠላቶቼም አልረገጡኝም። ነፍሴ ግን ደስታን አጣች። 3 እግዚአብሔርን ዐሰብሁት፥ ደስ አለኝም፤ ተናገርሁ፥ ነፍሴም ፈዘዘች። የጠላቶቼን ሁሉ ሰዓቶች ዐወቅኋቸው 4 ደነገጥሁ አልተናገርሁምም። 5 የድሮውን ዘመን ዐሰብሁ፤ የዘለዓለሙን ዓመታት ዐሰብሁ፤ አነበብኹም፤ 6 በሌሊት ከልቤ ጋር ተጫወትሁ፥ መንፈሴንም አነቃቃኋት። 7 እግዚአብሔር ለዘለዓለም በውኑ ይጥላልን? እንግዲህስ ይቅርታውን አይጨምርምን? 8 ለዘለዓለምስ ምሕረቱን ለልጅ ልጅ ይቈርጣልን? 9 እግዚአብሔር ይቅርታን ይረሳልን? በቍጣውስ ምሕረቱን ዘጋውን? 10 እነሆ፥ ዛሬ ጀመርሁ አልሁ፥ ልዑል ቀኙን እንደሚያፈራርቅ። 11 የእግዚአብሔርን ሥራ አስታወስሁ፤ የቀደመውን ተአምራትህን አስታውሳለሁና፤ 12 በምግባርህም ሁሉ እናገራለሁ፥ በሥራህም እጫወታለሁ። 13 አቤቱ፥ መንገድህ በመቅደስ ውስጥ ነው፤ እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው? 14 ተአምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ብቻ ነህ፤ ለሕዝብህ ኀይልህን አሳየሃቸው። 15 የያዕቆብንና የዮሴፍን ልጆች፥ ሕዝብህን በክንድህ አዳንሃቸው። 16 አቤቱ፥ ውኆች አዩህ፥ ውኆች አይተው ፈሩ፤ የውኆች ጥልቆች ተነዋወጡ፥ ውኆቻቸውም ጮኹ። 17 ደመናት ድምፅን ሰጡ፥ ፍላጾችህም ወጡ። 18 የነጐድጓድህ ድምፅ በሰረገላ ነበረ፤ መብረቆች ለዓለም አበሩ፤ ምድር ተናወጠች፥ ተንቀጠቀጠችም። 19 መንገድህ በባሕር ውስጥ ነው፥ ፍለጋህም በብዙ ውኆች ነው፥ ፍለጋህም አይታወቅም። 20 በሙሴና በአሮን እጅ ሕዝብህን እንደ በጎች መራሃቸው። |