መዝሙር 36 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዳዊት መዝሙር። 1 በክፉዎች ላይ አትቅና፥ ዐመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና፤ 2 እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፥ እንደ ለመለመ ቅጠልም ፈጥነው ይረግፋሉና። 3 በእግዚአብሔር ታመን፥ መልካምንም አድርግ፥ በምድርም ያሳድርሃል፥ በሀብትዋም ያሰማርሃል። 4 በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል። 5 መንገድህን ለአግዚአብሔር ግለጥ፥ በእርሱም ታመን፥ እርሱም ያደርግልሃል። 6 ጽድቅህን እንደ ብርሃን፥ ፍርድህንም እንደ ቀትር ያመጣታል። 7 ለእግዚአብሔር ተገዛ አገልግለውም። በሕይወቱ ደስ ባለውና ዐመፃን በሚያደርግ ሰው ላይ አትቅና። 8 መዓትን ተዋት፤ ቍጣንም ጣላት፥ እንዳትበድልም አትቅና። 9 ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። 10 ኀጢአተኛም ገና ጥቂት አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ፥ ቦታውንም አታገኝም። 11 የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፥ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል። 12 ኀጢአተኛ ጻድቁን ይመለካከተዋል፥ ጥርሱንም በእርሱ ላይ ያፋጫል። 13 እግዚአብሔር ግን ይሥቅበታል፥ ቀኑ እንደሚደርስ አስቀድሞ ዐውቆአልና። 14 ኃጥኣን ሰይፋቸውን መዘዙ፥ ቀስታቸውንም ገተሩ ድሃውንና ችግረኛውን ይገድሉ ዘንድ፥ ልበ ቅኖችንም ይወጉ ዘንድ፤ 15 ሰይፋቸው ወደ ልባቸው ይግባ፥ ቀስታቸውም ይሰበር። 16 በእውነት ያለ ጥቂት ከብዙ የኃጥኣን ሀብት ይበልጣል። 17 የኃጥኣን ኀይላቸው ይሰበራልና፤ እግዚአብሔር ጻድቃንን ይደግፋቸዋል። 18 የንጹሓንን መንገድ እግዚአብሔር ያውቃል፥ ርስታቸውም ለዘለዓለም ነው፤ 19 በክፉ ዘመንም አያፍሩም፤ በራብ ዘመንም ይጠግባሉ። 20 ኃጥኣን ግን ይጠፋሉ፤ የእግዚአብሔር ጠላቶች በከበሩና ከፍ ከፍ ባሉ ጊዜ እንደ ጢስ ይጠፋሉ። 21 ኀጢአተኛ ይበደራል፥ አይከፍልምም፤ ጻድቅ ግን ይራራል፥ ይሰጣልም። 22 እርሱን የሚባርኩት ምድርን ይወርሳሉና፤ የሚረግሙት ግን ይጠፋሉ። 23 የሰው አካሄዱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይጸናል፥ መንገዱንም እጅግ ይወድለታል። 24 ቢወድቅም አይደነግጥም፥ እግዚአብሔር እጁን ይዞ ይደግፈዋልና። 25 ጐለመስሁ፥ አረጅሁም፤ ጻድቅ ግን ሲጠፋ አላየሁም፤ ዘሩም እህልን አይቸገርም። 26 ሁልጊዜ ይራራል፤ ያበድራልም፤ ዘሩም በበረከት ይኖራል። 27 ከክፉ ሽሽ፥ መልካሙንም አድርግ፥ ለዘለዓለምም ትኖራለህ። 28 እግዚአብሔር ጽድቅን ይወድዳልና፥ ጻድቃኑንም አይጥላቸውምና፤ ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል፤ ለንጹሓንም ይበቀልላቸዋል፤ የኃጥኣንን ዘር ግን ያጠፋል። 29 ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፥ በእርስዋም ለዘለዓለም ይኖራሉ። 30 የጻድቅ አፉ ጥበብን ይማራል፥ አንደበቱም ጽድቅን ይናገራል። 31 የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው፥ ሰኰናውም አይሰናከልም። 32 ኀጢአተኛ ጻድቁን ይመለከተዋል፥ ሊገድለውም ይወድዳል። 33 እግዚአብሔር ግን በእጁ አይተወውም፥ በተፋረደውም ጊዜ አያሸንፈውም። 34 እግዚአብሔርን ደጅ ጥናው፥ መንገዱንም ጠብቅ፥ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ኃጥኣንም ሲጠፉ ታያለህ። 35 ኀጢአተኛን ከፍ ከፍ ብሎ፥ እንደ ሊባኖስ ዛፍም ረዝሞ አየሁት። 36 ብመለስ ግን አጣሁት፤ ፈለግሁት፥ ቦታውንም አላገኘሁትም። 37 ቅንነትን ጠብቅ፥ ጽድቅንም እይ፤ ለሰላም ሰው ቅሬት አለውና። 38 ዐመፀኞች ግን በአንድነት ይጠፋሉ፤ የኃጥኣንም ቅሬቶች ይጠፋሉ። 39 የጻድቃን መድኀኒታቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ በመከራቸውም ጊዜ ጠባቂያቸው እርሱ ነው። 40 እግዚአብሔር ይረዳቸዋል፥ ያድናቸዋልም፥ ከኃጥኣንም እጅ ያወጣቸዋል፥ ያድናቸዋልም፥ በእርሱ ታምነዋልና። |