ዘኍል 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የበለዓም የመጀመሪያው ትንቢት 1 በለዓምም ባላቅን፥ “ሰባት መሠዊያ በዚህ ሥራልኝ፤ ሰባትም ወይፈን፥ ሰባትም አውራ በግ በዚህ አዘጋጅልኝ” አለው። 2 ባላቅም በለዓም እንደ ተናገረ አደረገ፤ በየመሠዊያው ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረገ። 3 በለዓምም ባላቅን፥ “በመሥዋዕትህ ዘንድ ቈይ፤ እኔ እግዚአብሔር ቢገለጥልኝ፥ ቢገናኘኝም እሄዳለሁ፤ የሚገልጥልኝንም ቃል እነግርሃለሁ” አለው። ባላቅም በመሠዊያው ዘንድ ቆመ፤ በለዓም ግን እግዚአብሔርን ይጠይቅ ዘንድ አቅንቶ ሄደ። 4 እግዚአብሔርም ለበለዓም ታየው፤ በለዓምም ለእግዚአብሔር፥ “እነሆ፥ ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጀሁ፤ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረግሁ” አለው። 5 እግዚአብሔርም በበለዓም አፍ ቃልን አኖረ፤ “ወደ ባላቅ ተመለስ፤ እንዲህም በል” አለው። 6 ወደ እርሱም ተመለሰ፤ እነሆም፥ እርሱና የሞዓብ አለቆች ሁሉ በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ ወደ እርሱ መጣ፤ 7 በምሳሌም ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፦ “የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ ከምሥራቅ ተራሮች፤ ከሜስጴጦምያ ጠርቶ አመጣኝ፤ ና፥ ያዕቆብን ርገምልኝ፤ ና፥ እስራኤልን ተጣላልኝ” ብሎ። 8 እግዚአብሔር ያልረገመውን እንዴት እረግማለሁ? እግዚአብሔርስ ያልተጣላውን እንዴት እጣላለሁ? 9 በተራሮች ራስ ላይ ሆኜ አየዋለሁ፤ በኮረብቶችም ላይ ሆኜ እመለከተዋለሁ፤ እነሆ፥ ብቻውን የሚቀመጥ ሕዝብ ነው፤ በአሕዛብም መካከል አይቈጠርም። 10 የያዕቆብን ዘር ማን ያውቀዋል? የእስራኤልንስ ሕዝብ ማን ይቈጥረዋል? ሰውነቴም ከጻድቃን ሰውነት ጋር ትሙት፤ ዘሬም እንደ እነርሱ ዘር ትሁን።” 11 ባላቅም በለዓምን፥ “ያደረግኽብኝ ምንድን ነው? ጠላቶችን ትረግምልኝ ዘንድ ጠራሁህ፤ እነሆም፥ መባረክን ባረክሃቸው” አለው። 12 በለዓምም ባላቅን መልሶ፥ “በውኑ እግዚአብሔር በአፌ ያደረገውን እናገር ዘንድ የምጠነቀቅ አይደለምን?” የበለዓም ሁለተኛው ትንቢት 13 ባላቅም፥ “በዚያ እነርሱን ወደማታይበት ወደ ሌላ ቦታ እባክህ፥ ከእኔ ጋር ና፤ ከእነርሱ አንዱን ወገን ብቻ ታያለህ፤ ሁሉን ግን አታይም፤ በዚያም እነርሱን ርገምልኝ” አለው። 14 በሜዳ ወደ ተገነባ ግንብ ራስ ላይም ወሰደው፤ አዞረውም፤ ሰባትም መሠዊያዎች ሠራ፤ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈን፥ አንድም አውራ በግ አሳረገ። 15 በለዓምም ባላቅን አለው፥ “በዚህ በመሥዋዕትህ ዘንድ ቈይ፤ እኔም እግዚአብሔርን እጠይቅ ዘንድ እሄዳለሁ።” 16 እግዚአብሔርም በለዓምን ተገናኘው፤ ቃልንም በአፉ አኖረ፥ “ወደ ባላቅ ተመለስ፤ እንዲህም በለው።” 17 ወደ እርሱም መጣ፤ እነሆ፥ እርሱ ከእርሱም ጋር የሞዓብ አለቆች በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር፤ ባላቅም በለዓምን አለው፥ “እግዚአብሔር ምን አለ?” 18 በምሳሌም ይናገር ጀመር፤ እንዲህም አለ፦ “ባላቅ ሆይ፥ ተነሣ፤ ስማ፤ የሶፎር ልጅ ሆይ፥ ምስክር ሁነህ አድምጥ፤ 19 እግዚአብሔር እንደ ሰው የሚታለል አይደለም። እንደ ሰው ልጅም የሚዛትበት አይደለም፤ እርሱ ያለውን አያደርገውምን? አይናገረውምን? አይፈጽመውምን? 20 እነሆ፥ መጥቻለሁ፤ እባርካለሁ፤ አልመለስምም፤ 21 በያዕቆብ ላይ ድካም የለም፤ በእስራኤልም ሕማም አይታይም፤ አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው፤ የአለቆችም ክብር ለእርሱ ነው። 22 እግዚአብሔር ከግብፅ ያወጣው እርሱ ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ክብር ነው። 23 በያዕቆብ ላይ ጥንቆላ የለም፤ በእስራኤልም ላይ ምዋርት የለም፤ በየጊዜው ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል፦ እግዚአብሔር ምን አደረገ? ይባላል። 24 እነሆ፥ ሕዝቡ እንደ አንበሳ ደቦል ያገሣል፤ እንደ አንበሳም ይነሣል፤ ያደነውን እስኪበላ፥ የገደለውንም ደሙን እስኪጠጣ አይተኛም።” 25 ባላቅም በለዓምን አለው፥ “ከቶ አትርገማቸው፤ ከቶም አትባርካቸው።” 26 በለዓምም መልሶ ባላቅን አለው፥ “እግዚአብሔር የተናገረኝን ቃል ሁሉ አደርጋለሁ ብዬ አልተናገርሁህምን?” የበለዓም ሦስተኛው ትንቢት 27 ባላቅም በለዓምን አለው፥ “ና፥ ወደ ሌላ ስፍራ እወስድሃለሁ፤ ምናልባት በዚህ ሆነህ እነርሱን ትረግምልኝ ዘንድ እግዚአብሔር ይወድድ ይሆናል።” 28 ባላቅም በለዓምን በምድረ በዳ ወደ ተከበበው ወደ ፌጎር ተራራ ወሰደው። 29 በለዓምም ባላቅን፥ “በዚህ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፤ በዚህም ሰባት ወይፈን፥ ሰባትም አውራ በግ አዘጋጅልኝ” አለው። 30 ባላቅም በለዓም እንዳለው አደረገ፤ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረገ። |