ዘዳግም 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ታላቁ ትእዛዝ 1 “ልትወርሱአት በምትገቡባት ምድር ታደርጉት ዘንድ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንዳስተምራችሁ ያዘዘው ትእዛዝና ሥርዐት፥ ፍርድም ይህ ነው። 2 እናንተ፥ ልጆቻችሁም፥ የልጅ ልጆቻችሁም በዕድሜአችሁ ሁሉ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፈርታችሁ እኔ ለእናንተ ያዘዝሁትን ሥርዐቱንና ትእዛዙን ሁሉ ትጠብቁ ዘንድ፥ ዕድሜአችሁም ይረዝም ዘንድ፤ 3 እስራኤል ሆይ፥ ስማ፦ ማርና ወተት የምታፈስሰውን ምድር ይሰጥህ ዘንድ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ እጅግ እንድትበዛ፥ መልካምም እንዲሆንልህ ታደርጋት ዘንድ ጠብቅ።” ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ ሙሴ ለእስራኤል ልጆች በምድረ በዳ ያዘዛቸው ሥርዐትና ፍርድ ሁሉ ይህ ነው። 4 “እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ 5 አምላክህንም እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹምም ነፍስህ፥ በፍጹምም ኀይልህ ውደድ። 6 እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ፥ በነፍስህም ያዝ። 7 ለልጆችህም አስተምረው፤ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም አስተምረው። 8 በእጅህም እንደ ምልክት አድርገው፤ በዐይኖችህም መካከል እንደማይንቀሳቀስ ይሁንልህ። 9 በቤትህም መቃኖች፥ በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው። ስለ አለመታዘዝ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ 10 “አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተ ሊሰጣት ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ፥ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ባገባህ ጊዜ፤ ያልሠራሃቸውንም ታላቅና መልካም ከተሞች፥ 11 ያልሞላሃቸውንም ሀብትን የሞሉ ቤቶች፥ ያልማስሃቸውንም የተማሱ ጕድጓዶች፥ ያልተከልሃቸውንም ወይንና ወይራ በሰጠህ ጊዜ፥ በበላህና በጠገብህም ጊዜ፤ 12 ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ። 13 አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ፤ እርሱንም ተከተል በስሙም ማል። 14 በዙሪያችሁ ያሉት አሕዛብ የሚያመልኩአቸውን ሌሎች አማልክት አትከተሉ። 15 በመካከልህ ያለው አምላክህ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና የአምላክህ የእግዚአብሔር ቁጣ እንዳይነድድብህ፥ ከምድርም ፊት እንዳያጠፋህ ተጠንቀቅ። 16 “በፈተና ቀን እንደ ፈተንኸው አምላክህ እግዚአብሔርን አትፈታተነው። 17 ለአንተ ያዘዘውን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ፥ ምስክሩንም፥ ሥርዐቱንም አጥብቀህ ጠብቅ። 18 መልካምም ይሆንልህ ዘንድ፥ እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው ወደ መልካሚቱ ምድር ገብተህ እርስዋን ትወርስ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ቅኑንና መልካሙን አድርግ። 19 እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ጠላቶችህን ሁሉ ከፊትህ ያሳድድልህ ዘንድ። 20 “ነገ ልጅህ፦ አምላካችን እግዚአብሔር ያዘዛችሁ ምስክርና ሥርዐት፥ ፍርድስ ምንድን ነው? ብሎ በጠየቀህ ጊዜ፥ 21 አንተ ልጅህን በለው፦ በግብፅ የፈርዖን ባሪያዎች ነበርን፤ እግዚአብሔርም በጽኑ እጅ፥ በተዘረጋችም ክንድ ከዚያ አወጣን፤ 22 እግዚአብሔርም በግብፅና በፈርዖን በቤቱም ሁሉ ላይ በፊታችን ታላቅና ክፉ ምልክት፥ ተአምራትም አደረገ። 23 ለአባቶቻችን ወደ ማለላቸው ምድር ያገባንና እርስዋን ይሰጠን ዘንድ እኛን ከዚያ አወጣን። 24 እንደ ዛሬም በሕይወት እንዲያኖረን፥ ሁልጊዜም መልካም እንዲሆንልን፥ አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፈራ ዘንድ፥ ይህችንም ሥርዐት ሁሉ እናደርግ ዘንድ እግዚአብሔር አዘዘን። 25 እግዚአብሔርም እንዳዘዘን በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት እናደርጋት ዘንድ ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ብንጠብቅ ለእኛ ምሕረት ይሆንልናል።” |