ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ኢዮብ በእግዚአብሔር አመነ፤ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ማመስገንን ቸል አላለምና የአዳም ልጆች ጠላት ዲያብሎስ ካመጣበት መከራውም ሁሉ አዳነው፤ በደረሰበትም መከራ ልቡን አላሳዘነም፤ ነገር ግን “እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔርም ነሳ፤ እግዚአብሔርም እንደ ወደደ ሆነ፤ በሁሉም በሰማይና በምድር የእግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን” አለ። 2 እግዚአብሔርም የኢዮብ ልቡ ንጽሕት እንደ ሆነች ባየው ጊዜ፥ እግዚአብሔር በብዙ ክብር ተቀበለው። 3 ከቀደመ ገንዘቡ ይልቅ የሚበዛ ገንዘብንም ሰጠው፤ እጅግ ትዕግሥተኛ ሆኗልና፥ የደረሰበትን መከራ ሁሉ ስለ መታገሡ ከቍስሉ ፈወሰው። 4 እንዲሁም እናንተ ወደ እናንተ ከሚላኩ ጠላቶች ብትታገሡ ብፁዓን ትሆናላችሁ። 5 ታገሡ፤ እግዚአብሔር ከሚጠሏችሁ ሰዎች ለእናንተና ከእናንተም በኋላ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ መጠጊያ ይሆናችሁ ዘንድ ከመጣባችሁ መከራ የተነሣ ልቡናችሁን አታሳዝኑ፤ 6 እመኑት፥ እርሱም መጠጊያ ይሆናችኋል፤ ጥሩት፥ ይሰማችኋልም፤ ተስፋ አድርጉት፥ እርሱም ይቅር ይላችኋል፤ ለምኑት፥ እርሱም አባት ይሆናችኋል። 7 አስቴርንና መርዶክዮስን፥ ዮዲትንና ጌዴዎንንም፥ ባርቅንና ዲቦራንም፥ ሶምሶምንና ዮፍታሔንም፥ 8 በእግዚአብሔር ለማመን የጨከኑ ጠላቶቻቸውም ድል ያልነሷቸው እንደነርሱ ያሉ ሌሎችንም አስቡ። 9 እግዚአብሔር እውነተኛ ነውና፥ ፊት አይቶም አያዳላምና በእነርሱ ላይ ክፉ ያደርጉ ዘንድ የወደዱ ክፉውን ተቀበሉ፤ የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ግን ነፍሶቻቸውን ይጠብቃል፤ ክብርንና ባለሟልነትንም ይሰጣቸዋል። 10 በመግባታቸውና በመውጣታቸው፥ በሞታቸውና በሕይወታቸው፤ በመቀመጣቸውና በመነሣታቸውም ደስ ያሰኛቸዋል፤ እርሱ ያድናልና፥ ይገድላልምና። 11 እርሱ ይገርፋል፤ ይቅርም ይላል። 12 እርሱ ያደኸያል፤ ባለ ጸጋም ያደርጋል፤ እርሱ ያዋርዳል፥ ያከብራልም። |