2 ነገሥት 23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ንጉሡ ኢዮስያስ አምልኮ ጣዖትን እንደ አስወገደ ( 2ዜ.መ. 34፥3-7 ፤ 29-33 ) 1 ንጉሡም ላከ፤ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምንም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ እርሱ ሰበሰባቸው። 2 ንጉሡም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጣ፤ ከእርሱም ጋር የይሁዳ ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ሁሉ፥ ካህናቱና ነቢያቱም፥ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሾቹ ጀምሮ እስከ ታላቆቹ ድረስ ወጡ፤ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ በጆሮአቸው አነበበ። 3 ንጉሡም በዓምደ ወርቁ አጠገብ ቆሞ እግዚአብሔርን ይከተሉ ዘንድ፥ ትእዛዙንና ምስክሩንም ሥርዐቱንም በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ይጠብቁ ዘንድ፥ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል ያጸኑ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ፤ ሕዝቡም ሁሉ በቃል ኪዳን ጸኑ። 4 ንጉሡም የካህናቱን አለቃ ኬልቅያስን በሁለተኛውም መዓርግ ያሉትን ካህናት በረኞቹንም፥ ለበዓልና ለማምለኪያ ዐፀድ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ የተሠሩትን ዕቃዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር መቅደስ ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው፤ ከኢየሩሳሌምም ውጭ በቄድሮን ሜዳ አቃጠሉት፤ አመዱንም ወደ ቤቴል ወሰዱት። 5 የይሁዳ ነገሥታትም በይሁዳ ከተሞች በነበሩት በኮረብታው መስገጃዎች፥ በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ መስገጃዎች ያጥኑ ዘንድ ያኖሩአቸውን የጣዖቱን ካህናት፥ ለበዓልና ለፀሐይ፥ ለጨረቃና ለከዋክብት ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ያጥኑ የነበሩትን አቃጠላቸው። 6 የማምለኪያ ዐፀድንም ጣዖት ከእግዚአብሔር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም ውጭ ወደ ቄድሮን ፈፋ አወጣው፤ በቄድሮንም ፈፋ አጠገብ አቃጠለው፤ አድቅቆም ትቢያ አደረገው፥ ትቢያውንም በሕዝብ መቃብር ላይ ጨመረው። 7 ሴቶቹም ለማምለኪያ ዐፀድ መጋረጃ ይፈትሉባቸው የነበሩትን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያሉትን የሰዶማውያንን ቤቶች አፈረሰ። 8 ካህናቱንም ሁሉ ከይሁዳ ከተሞች አወጣቸው፤ ከጌባልም ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ካህናት ያጥኑበት የነበረውን የኮረብታ መስገጃ ሁሉ ርኩስ አደረገው። በከተማዪቱም በር በግራ በኩል በነበረው በከተማዪቱ ሹም በኢያሱ በር መግቢያ አጠገብ የነበሩትን የበሮቹን መስገጃዎች አፈረሰ። 9 የኮረብታው መስገጃዎች ካህናት ግን በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ አይመጡም ነበር፤ ብቻ በወንድሞቻቸው መካከል ቂጣ እንጀራ ይበሉ ነበር። 10 ሰው ሁሉ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን ለሞሎክ በእሳት እንዲሠዋ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ቆሞ የነበረውን ጣፌትን ርኩስ አደረገው። 11 የይሁዳም ነገሥታት በእግዚአብሔር ቤት መግቢያ አጠገብ በከተማው አቅራቢያ በነበረው በንጉሡ ጃንደረባ በናታን መኖሪያ አጠገብ ለፀሐይ የሰጡአቸውን ፈረሶች አቃጠለ፤ የፀሐይንም ሰረገሎች በእሳት አቃጠለ። 12 የይሁዳም ነገሥታት ያሠሩትን በአካዝ ቤት ሰገነት ላይ የነበሩትን መሠዊያዎች፥ ምናሴም ያሠራውን በእግዚአብሔር ቤት በሁለቱ ወለሎች ላይ የነበሩትን መሠዊያዎች ንጉሡ አስፈረሳቸው፤ ከዚያም አወረዳቸው፤ አደቀቃቸውም፥ ትቢያቸውንም በቄድሮን ፈፋ ጣለ። 13 በኢየሩሳሌምም ፊት ለፊት በርኵስት ተራራ ቀኝ የነበሩትን፥ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለሲዶናውያን ርኵስት ለአስታሮት፥ ለሞዓብም ርኵሰት ለካሞሽ፥ ለአሞንም ልጆች ርኵሰት ለሞሎክ ያሠራቸውን መስገጃዎች ንጉሡ ርኩስ አደረገ። 14 ሐውልቶቹንም ሁሉ አደቀቀ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ሁሉ ቈረጠ፤ በስፍራቸውም የሙታንን አጥንት ሞላበት። 15 ደግሞም በቤቴል ኮረብታ የነበረውን መሠዊያ፥ እስራኤልንም ያሳተ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ያሠራውን የኮረብታውን መስገጃ፥ ይህንም መሠዊያና መስገጃ አፈረሰ፤ ድንጋዮቹንም ሰባበረ፤ አድቅቆም ትቢያ አደረገው፤ የማምለኪያ ዐፀዱንም አቃጠለው። 16 ኢዮስያስም ዘወር ብሎ በከተማው የነበሩትን መቃብሮች አየ፤ ኢዮርብዓምም በበዓል ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ ልኮ ከመቃብሮቹ አጥንቶቹን አስወጣ፥ በመሠዊያው ላይም አቃጠላቸው፥ አረከሰውም። ዘወርም ብሎ ይህን ቃል ወደ ተናገረው ወደ እግዚአብሔር ሰው መቃብር ዐይኖቹን አቀና። እንዲህም አለ፦ 17 “ይህ የማየው የተቀበረ ነገር ምንድን ነው?” አለ የዚያችም ከተማ ሰዎች፥ “ከይሁዳ መጥቶ በቤቴል መሠዊያ ላይ ይህን ያደረግኸውን ነገር የተናገረው የእግዚአብሔር ሰው መቃብር ነው” ብለው ነገሩት። 18 እርሱም፥ “ተዉት፥ ማንም አጥንቱን አያንቀሳቅሰው” አለ፤ አጥንቶቹም ከሰማርያ ከመጣው ከነቢዩ አጥንት ጋር ዳኑ። 19 በሰማርያም ከተሞች የነበሩትን፥ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ የእስራኤል ነገሥታት የሠሩትን የኮረብታውን መስገጃዎች ኢዮስያስ አስወገዳቸው፤ በቤቴልም እንዳደረገው ነገር ሁሉ እንዲሁ አደረገባቸው። 20 በዚያም የነበሩትን የኮረብታውን መስገጃዎች ካህናት ሁሉ በመሠዊያዎቹ ላይ ገደላቸው፥ የሰዎቹንም አጥንት በመሠዊያዎቹ ላይ አቃጠለ። ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ። ኢዮስያስ የፋሲካን በዓል እንደ አደረገ ( 2ዜ.መ. 35፥1-19 ) 21 ንጉሡም ሕዝቡን ሁሉ፥ “በዚህ በቃል ኪዳኑ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ፋሲካን አድርጉ” ብሎ አዘዛቸው። 22 እንደዚህም ያለ ፋሲካ በእስራኤል ላይ ይፈርዱ ከነበሩ ከመሳፍንት ዘመን ጀምሮ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ አልተደረገም። 23 ነገር ግን በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ተደረገ። 24 ደግሞም ካህኑ ኬልቅያስ በእግዚአብሔር ቤት ባገኘው መጽሐፍ የተጻፈውን የሕጉን ቃል ያጸና ዘንድ፥ መናፍስት ጠሪዎቹንና ጠንቋዮቹን ተራፊምንና ጣዖታትንም በይሁዳ ሀገርና በኢየሩሳሌም የተገኘውን ርኵሰት ሁሉ ኢዮስያስ አስወገደ። 25 እንደ ሙሴም ሕግ ሁሉ በፍጹም ልቡ በፍጹምም ነፍሱ በፍጹምም ኀይሉ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ ከእርሱ አስቀድሞ አልነበረም፤ እንደ እርሱም ያለ ንጉሥ ከእርሱ በኋላ አልተነሣም። 26 ነገር ግን ምናሴ ስላስቈጣው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ከነደደው ከታላቁ ቍጣው ትኵሳት አልተመለሰም። 27 እግዚአብሔርም፥ “እስራኤልን እንዳራቅሁት ይሁዳን ከፊቴ አርቀዋለሁ፤ ይህችንም የመረጥኋትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና፦ ስሜ በዚያ ይሆናል ያልሁትንም ቤት እጥላለሁ” አለ። 28 የቀረውም የኢዮስያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 29 በእርሱም ዘመን የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ ከአሦር ንጉሥ ጋር ሊጋጠም ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ወጣ፤ ንጉሡም ኢዮስያስ ከእርሱ ጋር ሊጋጠም ወጣ፤ ፈርዖንም በተገናኘው ጊዜ በመጊዶ ገደለው። 30 አገልጋዮቹም በድኑን በሰረገላው አድርገው ከመጊዶ ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤ በመቃብሩም ቀበሩት። የሀገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ዮአክስን ወሰዱት። ቀብተውም በአባቱ ፋንታ አነገሡት። የዮአክስ ዘመነ መንግሥት ( 2ዜ.መ. 36፥2-4 ) 31 ዮአክስም በነገሠ ጊዜ ሃያ ሦስት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ። እናቱም አሚጣል ትባል ነበር፥ እርስዋም የሎብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 32 እርሱም አባቶቹ እንደ አደረጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 33 በኢየሩሳሌምም እንዳይነግሥ ፈርዖን ኒካዑ በኤማት ምድር ባለችው በዴብላታ አሰረው፤ በምድሩም ላይ መቶ መክሊት ብርና አንድ መቶ መክሊት ወርቅ ፈሰሴ ጣለበት። 34 ፈርዖን ኒካዑም የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስን ልጅ ኤልያቄምን በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ አነገሠ፤ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠው። ዮአክስንም ወስዶ ወደ ግብፅ አፈለሰው፤ በዚያም ሞተ። 35 ኢዮአቄምም ብሩንና ወርቁን ለፈርዖን ሰጠው፤ እንደ ፈርዖንም ትእዛዝ ገንዘብ ይሰጥ ዘንድ ምድሩን አስገበረ፤ ለፈርዖን ኒካዑም ግብር ይሰጥ ዘንድ ከሀገሩ ሕዝብ ሁሉ እንደ ግምጋሜው ብርና ወርቅ አስከፈለ። የኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት ( 2ዜ.መ. 36፥5-8 ) 36 ኢዮአቄምም በነገሠ ጊዜ ሃያ አምስት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ሄልድፍ ትባል ነበር፤ እርስዋም የሩማ ሰው የፈዳያ ልጅ ነበረች። 37 አባቶቹም እንዳደረጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። |