ዘኍል 15 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ መሥዋዕት አቀራረብ የተሰጠ ተጨማሪ ሕግ 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘እንድትኖሩባት ልሰጣችሁ ወዳቀድኩት ምድር በምትገቡበት ጊዜ፥ 3 ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ስለ ስእለት መፈጸም ለሚቀርብ መሥዋዕት ወይም በበጎ ፈቃድ ለሚቀርብ መሥዋዕት ወይም በተለመዱት የሃይማኖት በዓላት ላይ ለሚቀርብ መሥዋዕት፥ ከከብት ወይም ከበግ መንጋዎች ለእግዚአብሔር ታቀርባላችሁ፤ እንደዚህ ያለውም የምግብ ቊርባን መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል፤ 4 እንግዲህ እንደዚህ ያለውን መሥዋዕት የሚያቀርብ ሰው ሁሉ በሩብ ሊትር ዘይት የተለወሰ አንድ ኪሎ ምርጥ ዱቄት የእህል ቊርባንም ማቅረብ አለበት፤ 5 እንዲሁም ለያንዳንዱ ጠቦት ለመጠጥ ቊርባን የሚሆን ሩብ ሊትር የወይን ጠጅ ከሚቃጠል ቊርባን ወይም መሥዋዕት ጋር ታቀርባላችሁ። 6 አውራ በግ መሥዋዕት ሆኖ በሚቀርብበት ጊዜ ደግሞ በአንድ ሊትር ተኩል የወይራ ዘይት የተለወሰ ሁለት ኪሎ ዱቄት አቅርቡ፤ 7 ለመጠጥ ቊርባን የሊትር አንድ ሦስተኛ የወይን ጠጅ ታቀርባለህ፤ ይህም ሁሉ መሥዋዕት መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል፤ 8 ስለ ስእለት ወይም ስለ አንድነት አንድ ወይፈን ለሚቃጠል ቊርባን ወይም መሥዋዕት በምታቀርብበት ጊዜ፥ 9 ከወይፈኑ ጋር ሦስት ኪሎ በግማሽ ሊትር ዘይት የተለወሰ ምርጥ ዱቄት የእህል ቊርባን አቅርብ። 10 እንዲሁም ግማሽ ሊትር የወይን ጠጅ የመጠጥ ቊርባን አድርገህ ታቀርባለህ፤ ይህም ለእግዚአብሔር መልካም መዓዛ የሚሆን የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። 11 “ ‘እንግዲህ ከእያንዳንዱ ወይፈን፥ አውራ በግ፥ የበግ ወይም የፍየል ጠቦት ጋር የሚቀርበው የእህል ቊርባን ይህ ነው፥ 12 ከአንድ እንስሳ በላይ በሚቀርብበት ጊዜ አብሮት የሚቀርበውም የእህል ቊርባን በተመሳሳይ ሁኔታ ይጨምራል፤ 13 የአገር ተወላጅ የሆነ እያንዳንዱ እስራኤላዊ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የእህል ቊርባን በሚያቀርብበት ጊዜ ይህን ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል፤ 14 ከእናንተ ጋር ያለ ወይም በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ ቊርባን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ ቢፈልግ፥ ይህንኑ የሥርዓት መመሪያ በተመሳሳይ ሁኔታ መከተል ይኖርበታል። 15 እናንተም ሆናችሁ በመካከላችሁ የሚኖሩ መጻተኞች ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ እነዚህን የሥርዓት መመሪያዎች በተመሳሳይ ሁኔታ መጠበቅ ይኖርባችኋል፤ እናንተም ሆናችሁ እነርሱ በእግዚአብሔር ፊት አንድ ናችሁ። 16 ማንኛውም ሕግና የሥርዓት መመሪያ ለሁላችሁም እኩል ነው።’ ” 17 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 18 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ ወደምመራችሁ ምድር በምትገቡበት ጊዜ፥ 19 ከምድሪቱ የሚመረተውን ነገር ሁሉ በምትመገቡበት ወቅት ከእርሱ ላይ ጥቂት በማንሣት ለእግዚአብሔር ልዩ ስጦታ አድርጋችሁ አቅርቡ፤ 20 ይኸውም ከአዲስ እህል የተጋገረው የመጀመሪያው ኅብስት ለእግዚአብሔር ልዩ መባ ሆኖ ይቅረብ፤ ይህም ከምትወቁት እህል በማንሣት እንደምታመጡት ልዩ መባ በተመሳሳይ ይቅረብ፤ 21 ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ ከአዲስ እህል ከምትጋግሩት ኅብስት እየተነሣ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ ሆኖ መቅረብ አለበት። 22 “ምናልባት እናንተ ሆን ብላችሁ ሳይሆን ባለማወቅ እግዚአብሔር ለሙሴ ከሰጠው ትእዛዞች መካከል አንዱን ሳትጠብቁ ብትቀሩ፥ 23 ወይም ምናልባት ወደፊት ዘሮቻችሁ በሙሴ አማካይነት ያዘዘውን ትእዛዝ ሁሉ ሳይፈጽሙ ቢቀሩ፥ 24 እንዲህ ዐይነቱ ስሕተት የተፈጸመው በማኅበሩ አለማወቅ ከሆነ አንድ ወይፈን አምጥተው መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ያቅርቡት፤ ከእርሱም ጋር ተገቢውን የእህልና የወይን ጠጅ ቊርባን ያቅርቡ፤ በተጨማሪም አንድ ተባዕት ፍየል ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አድርገው ያቅርቡ። 25 ካህኑም ለመላው የእስራኤል ማኅበር ያስተስርይላቸው፤ ስሕተቱን የፈጸሙት ባለማወቅ ስለ ሆነና ስለ ኃጢአት ስርየት የሚሆነውንም መሥዋዕትና የእህል ቊርባን አድርገው ለእግዚአብሔር ስላቀረቡ፥ ኃጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል። 26 ሁሉም በአንድነት የስሕተቱ ተካፋዮች ስለ ሆኑ መላው የእስራኤል ማኅበርና በእነርሱም መካከል የሚኖሩ መጻተኞች ኃጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል። 27 “አንድ ሰው በግሉ ባለማወቅ ኃጢአት ቢሠራ አንድ ዓመት የሞላት እንስት ፍየል ስለ ኃጢአቱ ስርየት መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። 28 ካህኑ በስሕተት ኃጢአት ለሠራው ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያስተስርይለት፤ ኃጢአቱም ይቅር ይባልለታል። 29 የአገር ተወላጅ እስራኤላዊም ሆነ ወይም በዚያ የሚኖር መጻተኛ ባለማወቅ ኃጢአት የሚሠራ ሁሉ የሚከተለው ሕግ ይኸው ነው። 30 “ነገር ግን የአገሩ ተወላጅም ሆነ መጻተኛ፥ ሆን ብሎ ኃጢአት የሚሠራ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ የንቀት ዝንባሌ በማሳየቱ ከሕዝቡ ይለይ፤ 31 ይህም የሚደርስበት እግዚአብሔር የተናገረውን ችላ ስላለና ከትእዛዞቹም አንዱን ሆን ብሎ ስለ ጣሰ ነው፤ ስለዚህ ያ ሰው ፈጽሞ ይጥፋ፤ ኀላፊነቱ የራሱ ነው።” ሰንበትን በመሻር የተቀጣው ሰው 32 እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ አንድ ጊዜ አንድ ሰው በሰንበት ቀን የማገዶ እንጨት ሲለቅም ተያዘ፤ 33 የያዙትም ሰዎች መላው ማኅበር ወዳለበት ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወሰዱት። 34 በእርሱ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ግልጥ ሆኖ ስላልተገኘ ለጊዜው በዘብ ተጠብቆ እንዲቈይ ተደረገ፤ 35 ከዚያን በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን “ሰውየው መገደል አለበት፤ መላው ማኅበር ከሰፈር አውጥተው በድንጋይ ወግረው ይግደሉት” አለው። 36 ስለዚህ መላው ማኅበር ከሰፈር አውጥተው እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ስለ ልብስ ዘርፍ የተሰጠ መመሪያ 37 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 38 “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በልብሶቻችሁ ጫፍ ላይ ሁሉ ዘርፍ አብጁ፤ እያንዳንዱም ዘርፍ ከሰማያዊ ፈትል የተሠራ ጥለት ይኑረው፤ ይህንንም ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ አድርጉ፤ 39 ዘርፎቹም እንደማስታወሻ ሆነው ስለሚያገለግሉ፥ እነርሱን በምታዩበት ጊዜ ሁሉ ትእዛዞቼን በማስታወስ ትፈጽማላችሁ፤ ከእኔም ርቃችሁ የገዛ ፈቃዳችሁንና ምኞታችሁን የምትፈጽሙ አትሆኑም፤ 40 በልብሶቻችሁም ጫፍ ላይ የሚታዩት ዘርፎች ትእዛዞቼን ሁሉ እንድትፈጽሙ ያስታውሱአችኋል፤ እናንተም በፍጹም ለእኔ የተገዛችሁ ትሆናላችሁ። 41 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ፥ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ” |