Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

1 ዜና መዋዕል 16 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ታቦቱ በመገናኛ ድንኳን ውስጥ መቀመጡ

1 የእግዚአብሔርንም ታቦት ይዘው ገቡ፥ ዳዊትም በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕትም በጌታ ፊት አቀረቡ።

2 ዳዊትም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነቱን መሥዋዕት አቅርቦ በፈጸመ ጊዜ በጌታ ስም ሕዝቡን ባረከ።

3 ለእስራኤልም ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ፥ አንዳንድም ቁራጭ ሥጋ፥ አንዳንድም የዘቢብ ጥፍጥፍ አከፋፈለ።

4 በጌታም ታቦት ፊት እንዲያገለግሉ፥ የእስራኤልንም አምላክ ጌታን እንዲወድሱት፥ እንዲያመሰግኑትና እንዲያከብሩትም ከሌዋውያን ወገን ሾመ።

5 አለቃው አሳፍ ነበረ፤ ከእርሱም ቀጥሎ መሰንቆና በገና ይጫወቱ የነበሩት ዘካርያስ፥ ይዒኤል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ መቲትያ፥ ኤልያብ፥ በናያስ፥ ዖቤድ-ኤዶም፥ ይዒኤል ነበሩ፤ አሳፍም የጸናጽልን ድምፅ ያሰማ ነበረ።

6 ካህናቱም በናያስና የሕዚኤል በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ሁልጊዜ መለከት ይነፉ ነበር።


የዳዊት የምስጋና ዝማሬ

7 በዚያም ቀን ዳዊት በአሳፍና በወንድሞቹ አንደበት ጌታን እንዲያመሰግኑ አስቀድሞ ትእዛዝን ሰጠ።

8 ጌታን አመስግኑ፥ ስሙን ጥሩ፤ ለአሕዛብ ሥራውን አውሩ።

9 ተቀኙለት፥ ዘምሩለት፤ ተአምራቱንም ሁሉ ተናገሩ።

10 በቅዱስ ስሙ ክብር ይሁን፤ ጌታን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው።

11 ጌታን ፈልጉት፥ ብርታቱን እሹ፤ ሁልጊዜ ፊቱን ፈልጉ።

12 ተአምራቱንም የተናገረውንም ፍርድ፥ የሠራትን ድንቅ አስቡ፤ እናንተ

13 ባርያዎቹ የሆናችሁ የእስራኤል ዘር ሆይ! ለእርሱም የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ!

14 እርሱ ጌታ አምላካችን ነው፤ ፍርዱ በምድር ሁሉ ነው።

15 ቃል ኪዳኑን ለዘለዓለም፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን አሰበ፥

16 ለአብርሃም ያደረገውን፥ ለይስሐቅም የማለውን፤

17 ለያዕቆብ ሥርዓት እንዲሆን ለእስራኤልም የዘለዓለም ኪዳን እንዲሆን አጸና፤

18 እንዲህም አለ፦ “ለአንተ የከነዓንን ምድር የርስታችሁን ድርሻ እሰጣለሁ፤”

19 ይህም የሆነው እነርሱ በቍጥር ጥቂቶች ሰዎች፥ እጅግ ጥቂቶችና ስደተኞች በነበሩ ጊዜ ነው።

20 ከአንድ ሕዝብ ወደ ሌላ ሕዝብ፥ ከአንድም መንግሥት ወደ ሌላ ሕዝብ ተንከራተቱ።

21 ማንም ሰው ግፍ እንዲያደርግባቸው አልፈቀደም፤ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ።

22 እንዲህም አለ፦ “የቀባኋቸውን አትንኩ፤ በነቢያቴ ክፉ አታድርጉ።”

23 ምድር ሁሉ ጌታን አመስግኑ፤ ዕለት ዕለት ማዳኑን አውሩ።

24 ክብሩን ለአሕዛብ፥ ተአምራቱንም ለሰዎች ሁሉ ንገሩ።

25 ጌታ ታላቅ፥ ከፍ ያለ ምስጋናም ይገባዋልና፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ የተፈራ ነው።

26 የአሕዛብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤ ጌታ ግን ሰማያትን ሠራ።

27 ክብርና ግርማ በፊቱ፥ ኃይልና ደስታ በስፍራው ውስጥ ናቸው።

28 የአሕዛብ ወገኖች ለጌታ የሚገባውን ስጡ፥ ለጌታ ተገቢውን ክብርና ኃይል ስጡ።

29 ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር ስጡ፤ ቁርባንን ይዛችሁ በፊቱ ግቡ፤ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ።

30 ምድር ሁሉ በፊቱ ትናወጥ፤ ዓለሙም ፍጹም እንዳይናወጥ በጽኑ ይታነጻል።

31 ሰማያት ደስ ይበላቸው፥ ምድርም ሐሤትን ታድርግ፤ በአሕዛብም መካከል፦ “ጌታ ነግሷል” ይበሉ።

32 ባሕርና ሞላዋ በጩኽት ያስገምግሙ፤ በረሀ በእርሷም ያሉ ሁሉ ሐሤትን ያድርጉ።

33 በምድር ሊፈርድ ይመጣልና፥ የዱር ዛፎች በዚያን ጊዜ በጌታ ፊት ደስ ይላቸዋል።

34 መልካም ነውና፥ ጽኑ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና ጌታን አመስግኑ።

35 እንዲህም በሉ፦ “የመዳናችን አምላክ ሆይ! አድነን፤ ቅዱስ ስምህን እንድናመሰግን፥ በምስጋናህም እንድንከብር፥ ከአሕዛብ መካከል ሰብስበኸን ታደገን።

36 ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም፥ የእስራኤል አምላክ ጌታ ይባረክ።” ሕዝቡም ሁሉ “አሜን” አሉ፤ ጌታንም አመሰገኑ።


ዘውትር የሚደረገው አምልኮ አለመቋረጡ

37 እንዲሁም ንጉሥ ዳዊት በየቀኑ እንደሚገባቸው በታቦቱ ፊት ዘወትር እንዲያገለግሉ አሳፍንና ወንድሞቹን፥ ዖቤድ-ኤዶምንም፥ ስልሳ ስምንቱንም ወንድሞቻቸውን በዚያ በጌታ ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ተዋቸው።

38 የኤዶታምም ልጅ ዖቤድ-ኤዶምና ሖሳ የደጁ ጠባቂዎች እንዲሆኑ አድርጎ ከስልሳ ስምንት ወድሞቹ ጋር ዖቤድ-ኤዶምን በዚያ ተወው።

39 ካህኑን ሳዶቅንና ካህናቱን ወንድሞቹን በገባዖን በኮረብታው መስገጃ ባለው በጌታ ማደሪያ ፊት እንዲያገለግሉ በዚያ ተዋቸው፤

40 በዚያም ለእስራኤልም ባዘዘው በጌታ ሕግ እንደ ተጻፈ ሁሉ ለሚቃጠለው መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁልጊዜ ጥዋትና ማታ ለጌታ ያቀርባሉ።

41 ጽኑ ፍቅሩም ለዘለዓለም ነውና ጌታን እንዲያመሰግኑ ኤማንንና ኤዶታምን፥ በስማቸውም የተጻፉትን ተመርጠው የቀሩትን ከእነርሱ ጋር በዚያ ተዋቸው።

42 ከእነርሱም ጋር ካህናቱ ከፍ አድርገው ለማሰማት መለከትና ጸናጽል ለእግዚአብሔርም መዝሙራት የዜማ ዕቃ ይዘው ነበር፤ የኤዶታምም ልጆች ጠባቂዎች ነበሩ።

43 ሕዝቡ ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ቤቱ ሄደ፤ ዳዊትም ቤተሰቡን ለመባረክ ወደ ቤቱ ተመልሶ ሄደ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች