የእግዚአብሔር ታቦት ከአሚናዳብ ቤት ወደ ኢየሩሳሌም እንደ መጣች( 1ዜ.መ. 13፥1-14 ፤ 15፥25—16፥6፤43 ) 1 ዳዊትም ደግሞ ከእስራኤል የተመረጡትን ሰባ ሺህ ያህል ሰው ሰበሰበ። 2 ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ከይሁዳ አለቆች ጋር ተነሥተው በኪሩቤል ላይ የተቀመጠ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ስም የተጠራባትን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያመጡ ዘንድ ሄዱ። 3 የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሰረገላ ላይ ጫኑአት፥ በኮረብታውም ላይ ከነበረው ከአሚናዳብ ቤት አመጡአት፤ የአሚናዳብ ልጆችም ዖዛና ወንድሞቹ ታቦቷ ያለችበትን ሰረገላ ይነዱ ነበር። 4 ወንድሞቹም በታቦቷ ፊት ይሄዱ ነበር። 5 ዳዊትና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በዜማ መሣሪያዎች በበገናና በመሰንቆ፥ በከበሮና በነጋሪት፥ በጸናጽልና በዕንዚራ በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኀይላቸው ይጫወቱ ነበር። 6 ወደ ናኮንም አውድማ ደረሱ፤ ዖዛም በሬዎቹ አነቃንቀዋት ነበርና ይይዛት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ታቦት እጁን ዘረጋ፤ አስተካከላትም። ሲይዛትም በሬው ወጋው። 7 እግዚአብሔርም በዖዛ ላይ ተቈጣ፤ እግዚአብሔርም በዚያው ቀሠፈው። በእግዚአብሔርም ታቦት አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት በዚያው ሞተ። 8 እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ገደለው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያ ስፍራ ስም “ዖዛ የሞተበት” ተባለ። 9 በዚያም ቀን ዳዊት እግዚአብሔርን ፈራና፥ “የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ትገባለች?” አለ። 10 ዳዊትም የእግዚአብሔርን ታቦተ ሕግ ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ ያመጣት ዘንድ አልወደደም፤ ዳዊትም በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት አገባት። 11 የእግዚአብሔርም ታቦት በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ተቀመጠች፤ እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤቱን ሁሉ ባረከ። 12 ለንጉሡ ዳዊትም “እግዚአብሔር የአቢዳራን ቤትና የነበረውን ሁሉ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ባረከ” ብለው ነገሩት። ዳዊትም ሄዶ የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በደስታ አመጣት። 13 ከእርሱም ጋር የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙ ሰባት መሰንቆ የሚመቱ ክፍሎች ነበሩ። በሬዎችንና በጎችን ይሠዉ ነበር። 14 ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት በገና ይደረድር ነበር፤ ዳዊትም ለዐይን የሚያንጸባርቅ የሐር ቀሚስ ለብሶ ነበር። 15 ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በእልልታ ቀንደ መለከት እየነፉ የእግዚአብሔርን ታቦት አመጡአት። 16 የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በደረሰች ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡም ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘምር አየችው፥ በልብዋም ናቀችው። 17 የእግዚአብሔርንም ታቦት አምጥተው ዳዊት በተከለላት ድንኳን ውስጥ በስፍራዋ አኖሩአት፤ ዳዊትም የሚቃጠልና የሰላም መሥዋዕትን በእግዚአብሔር ፊት አሳረገ። 18 ዳዊትም የሚቃጠልና የሰላም መሥዋዕት ማሳረግን ከፈጸመ በኋላ ሕዝቡን በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም መረቀ። 19 ለሕዝቡም ሁሉ ለእስራኤል ወገን ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ለወንዱም፥ ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ፥ አንዳንድም የሥጋ ቍራጭ፥ አንዳንድም ጽዋዕ ወይን አከፋፈለ። ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ቤቱ ሄደ። 20 ዳዊትም ቤተ ሰቡን ሊመርቅ ተመለሰ። የሳኦል ልጅ ሜልኮልም ዳዊትን ለመቀበል ወጣችና ሰላምታ ሰጠችው፥ “ከሚዘፍኑት አንዱ እንደሚገለጥ የእስራኤል ንጉሥ በአገልጋዮቹ ሚስቶች ፊት በመገለጡ ምንኛ የተከበረ ነው!” አለች። 21 ዳዊትም ሜልኮልን፥ “በእግዚአብሔር ፊት ዘምሬአለሁ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እጫወታለሁ፤ እዘምራለሁም፤ 22 አሁንም እገለጣለሁ፤ በዐይንሽ ፊትና እንዴት ከበርህ ባልሽባቸው ሴቶች ልጆች ፊት የተናቅሁ እሆናለሁ” አላት። 23 የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም። |