2 ሳሙኤል 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዳዊት የእግዝ!አብሔርን ቤት ለመሥራት እንደ አሰበ ( 1ዜ.መ. 17፥1-15 ) 1 እንዲህም ሆነ፤ ንጉሡ በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ እግዚአብሔርም በዙሪያው ያሉ ጠላቶቹን ሁሉ ባወረሰው ጊዜ፥ 2 ንጉሡ ነቢዩ ናታንን፥ “እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጬአለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ተቀምጣለች” አለው። 3 ናታንም ንጉሡን፥ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና፥ ሂድና በልብህ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” አለው። 4 በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ፤ እንዲህም አለው፦ 5 “ሂድ ለባሪያዬ ለዳዊት ንገረው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም። 6 የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ እሄድና እመላለስ ነበር እንጂ በቤት አልተቀመጥሁምና፥ 7 ከእስራኤል ልጆች ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ፦ ስለምን ቤትን ከዝግባ እንጨት አልሠራችሁልኝም? ብዬ ሕዝቤን እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ላዘዝሁት ለአንዱ በውኑ ተናግሬአለሁን? 8 አሁንም ዳዊትን ባሪያዬን እንዲህ በለው፦ ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ፤ 9 በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፤ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆቹ ስም ስምህን ታላቅ አደረግሁ። 10 ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርጋለሁ፤ እተክላቸውማለሁ፤ ብቻቸውን ይቀመጣሉ፤ ከዚያም በኋላ የሚጠራጠሩት የለም፤ እንደ ቀድሞው ዘመን የኀጢአት ልጅ መከራ አያጸናባቸውም። 11 በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ፈራጆችን በሾምሁ ጊዜ ከጠላቶችህ ሁሉ አሳርፍሃለሁ። እግዚአብሔርም ደግሞ፦ ቤት እንደምትሠራለት ይነግርሃል፤ እሠራለታለሁ ብለሃልና። 12 ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ፤ ከአባቶችህም ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ፥ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፤ መንግሥቱንም አዘጋጃለሁ ። 13 እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፤ ዙፋኑን ለዘለዓለም አጸናለሁ። 14 እኔም አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ክፉ ነገርም ቢያደርግ፥ በሰዎች በትርና በሰው ልጆች አለንጋ እገሥጸዋለሁ፤ 15 ከፊቴም ከጣልሁት ከሳኦል ቤት እንዳራቅሁ ምሕረቴን ከእርሱ አላርቅም። 16 ቤቱ የታመነ ይሆናል፤ መንግሥቱም በፊቴ ለዘለዓለም፥ ዙፋኑም ለዘለዓለም ይጸናል።” 17 እንደዚህ ቃል ሁሉ፥ እንደዚህም ራእይ ሁሉ ናታን ለዳዊት እንዲሁ ነገረው። የዳዊት የምስጋና ጸሎት ( 1ዜ.መ. 17፥16-27 ) 18 ንጉሡ ዳዊትም ገባ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፥ “ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህን ያህል የወደድኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድን ነው? 19 ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ እኔ በፊትህ እጅግ ታናሽ ስሆን ስለ ባሪያህ ቤት ደግሞ ለሩቅ ዘመን ተናገርህ፤ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ የሰው ሕግ ነው። 20 ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ባሪያህን ታውቃለህና ዳዊትስ ይናገርህ ዘንድ የሚጨምረው ምንድን ነው? 21 ለባሪያህም ታስታውቀው ዘንድ ስለ ቃልህ ምክንያትና እንደ ልብህ አሳብ ይህን ታላቅ ነገር ሁሉ አደረግህ። 22 ስለዚህም አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እንዳንተ ያለ የለምና፥ በጆሮአችንም እንደ ሰማን ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለምና አንተ ታላቅ ነህ። 23 ለእርሱ ለራሱ እንዲሆን ሕዝብን ይቤዥ ዘንድ ለእርሱ ለራሱም ታላቅ ስምን ያደርግ ዘንድ አሕዛብንና ሰፈሮቻቸውን በመበተን ከግብፅ በተቤዠኸው ሕዝብህ ፊት ታምራትንና ድንቅን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ መራው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ምን ሕዝብ አለ? 24 ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘለዓለም ሕዝብ አድርገህ አዘጋጅተኸዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ አምላክ ሆነሃቸዋል። 25 አቤቱ ሁሉን የምትገዛ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አሁንም ለባሪያህና ለቤቱ የተናገርኸውን ለዘለዓለም አጽናው፤ አሁንም እንደ ተናገርህ አድርግ። 26 ስምህ ለዘለዓለም ታላቅ ይሁን። 27 አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ ሆይ፥ የባሪያህን ጆሮ ከፈትህ። አንተ፦ እኔ ቤት እሠራልሃለሁ አልህ፤ ስለዚህም ባሪያህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ይጸልይ ዘንድ በልቡ አሰበ። 28 ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አሁንም አንተ አምላክ ነህ፤ ቃልህም እውነት ነው፤ ይህንም መልካም ነገር ለባሪያህ ተናግረሃል። 29 ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ተናግረሃልና አሁን እንግዲህ ለዘለዓለም በፊትህ ይሆን ዘንድ የባሪያህን ቤት እባክህ ባርክ፤ በበረከትህም የባሪያህ ቤት ለዘለዓለም ይባረክ።” |