ነህምያ 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የሕዝቡም አለቆች በኢየሩሳሌም ተቀመጡ፤ ከቀሩትም ሕዝብ ከዐሥሩ ክፍል አንዱ በቅድስቲቱ ከተማ በኢየሩሳሌም፥ ዘጠኙም በሌሎች ከተሞች ይቀመጡ ዘንድ ዕጣ ተጣጣሉ። 2 ሕዝቡም በፈቃዳቸው በኢየሩሳሌም ለመቀመጥ የወደዱትን ሰዎች ሁሉ ባረኩ። 3 በኢየሩሳሌምም የተቀመጡት የሀገሩ አለቆች እነዚህ ናችው፤ እስራኤል ግን ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም፥ ናታኒምም፥ የሰሎሞንም አገልጋዮች ልጆች እያንዳንዳቸው በየርስታቸውና በየከተማቸው በይሁዳ ከተሞች ተቀመጡ። 4 ከይሁዳና ከብንያምም ልጆች እነዚህ በኢየሩሳሌም ተቀመጡ። ከይሁዳ ልጆች፤ ከፋሬስ ልጆች የመላልኤል ልጅ፥ የሰፋጥያስ ልጅ፥ የሰማርያ ልጅ፥ የዘካርያስ ልጅ፥ የዖዝያ ልጅ አታያ፤ 5 የሴሎ ልጅ፥ የዘካርያስ ልጅ፥ የዮያሪብ ልጅ፥ የዓዳያ ልጅ፥ የዖዝያ ልጅ፥ የኮልሖዜ ልጅ፥ የባሩክ ልጅ መዕሤያ። 6 በኢየሩሳሌም የተቀመጡት የፋሬስ ልጆች ሁሉ አራት መቶ ስድሳ ስምንት ጽኑዓን ነበሩ። 7 የብንያምም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ የይሳዕያ ልጅ፥ የአትያል ልጅ፥ የመዕሤያ ልጅ፥ የቆላያ ልጅ፥ የፈዳያ ልጅ፥ የዮሐድ ልጅ፥ የሜሱላም ልጅ ሴሎ። 8 ከእርሱም በኋላ ጌቤና ሴል ዘጠኝ መቶ ሃያ ስምንት ነበሩ። 9 አለቃቸውም የዝክሪ ልጅ ኢዮኤል ነበረ፤ የሰኑዋም ልጅ ይሁዳ በከተማው ላይ ሁለተኛ ነበረ። 10 ከካህናቱም የዮያሬብ ልጅ ይዳእያና ያኪን፤ 11 የእግዚአብሔርም ቤት አለቃ የአኪጦብ ልጅ፥ የማርዮት ልጅ፥ የሳዶቅ ልጅ፥ የሜሱላም ልጅ፥ የኬልቅያስ ልጅ ሣርያ፥ 12 የእግዚአብሔርንም የቤቱን ሥራ የሠሩ ወንድሞቻቸው ስምንት መቶ ሃያ ሁለት የመልክያ ልጅ፥ የፋስኩር ልጅ፥ የዘካርያስ ልጅ፥ የአማሴ ልጅ፥ የፈላልያ ልጅ፥ የይሮሖም ልጅ ዓዳያ፥ 13 ወንድሞቹም የአባቶች ቤቶች አለቆች ሁለት መቶ አርባ ሁለት፤ የኢሜር ልጅ፥ የሜሱላሙት ልጅ፥ የአሐዚ ልጅ፥ የኤዝርኤል ልጅ ሐማስያ፥ 14 ወንድሞቻቸውም መቶ ሃያ ስምንት ጽኑዓን ኀያላን፤ አለቃቸውም የሐጊዶሌም ልጅ ዘብዲሔል ነበረ። 15 ከሌዋውያንም የቡኒ ልጅ፥ የአሳብያ ልጅ፥ የዓዝሪቃም ልጅ፥ የሐሱብ ልጅ ሰማያ፤ 16 ከእግዚአብሔርም ቤት በውጭ በነበረው ሥራ ላይ የነበሩ የሌዋውያን አለቆች ሴቤታይና ኢዮዛብድ፤ 17 በጸሎትም ጊዜ ምስጋናን የሚጀምሩ አለቃው የአሳፍ ልጅ፥ የዛብዲ ልጅ፥ የሚካ ልጅ ማታንያ፥ በወንድሞቹም መካከል ሁለተኛ የነበረ ቦቂቦቅያ፥ የኢዶትም ልጅ፥ የጌላል ልጅ፥ የሰሙዓ ልጅ አብድያ። 18 በቅድስቲቱ ከተማ የነበሩ ሌዋውያን ሁሉ ሁለት መቶ ሰማንያ አራት ነበሩ። 19 በሮቹንም የሚጠብቁ በረኞች፥ ዓቁብና ጤልሞን፥ ወንድሞቻቸውም መቶ ሰባ ሁለት ነበሩ። 20 ከእስራኤልም የቀሩት ከካህናትና ከሌዋውያንም እያንዳንዳቸው በየርስታቸው በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ውስጥ ነበሩ። 21 ናታኒምም በዖፌል ተቀምጠው ነበር፤ ሲሐና ጊስፋም በናታኒም ላይ ነበሩ። 22 በእግዚአብሔርም ቤት ሥራ ላይ ከነበሩ መዘምራን ከአሳፍ ልጆች ወገን የሚካ ልጅ፥ የመታንያ ልጅ፥ የሐሳብያ ልጅ፥ የባኒ ልጅ ኦዚ በኢየሩሳሌም የሌዋውያን አለቃ ነበረ። 23 በእነርሱም ላይ የንጉሥ ትእዛዝ ነበረ፤ የመዘምራኑም ሥርዐት ለየዕለቱ የተሠራ ነበረ። 24 ከይሁዳም ልጅ ከዛራ ወገን የባስያዘብኤል ልጅ ፈታያ ስለ ሕዝቡ ነገር ሁሉ በንጉሡ አጠገብ ነበረ። 25 ስለ መንደሮቹና ስለ እርሻዎቻቸው ከይሁዳ ልጆች ዐያሌዎች በቂርያትአርባቅና በመንደሮችዋ፥ በዲቦንና በመንደሮችዋም፥ በቃጽብኤልና በመንደሮችዋም፥ 26 በኢያሱ፥ በሞላዳ፥ በቤተፋሌጥ፥ 27 በሐጸርሱዓል፥ በቤርሳቤህና በመንደሮችዋ፥ 28 በጼቅላቅ፥ በመኮናና በመንደሮችዋ፥ 29 በዓይንሪሞን፥ በጼርህ፥ በየርሙት፥ 30 በዛኖህ፥ በዓዶላም፥ በመንደሮቻቸውም፥ በለኪሶና በእርሻዎችዋ፥ በዓዜቃና በመንደሮችዋ ተቀመጡ። እንዲሁ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ሄኖም ሸለቆ ድረስ ሰፈሩ። 31 የብንያምም ልጆች ከጌባ ጀምሮ በማኬማስ፥ በአያል፥ በቤቴልና በመንደሮችዋ፥ 32 በዓናቶት፥ በኖብ፥ በሐናንያ፥ 33 በሐጾር፥ በራማ፥ በጌትም፤ 34 በሐዲድ፥ በሰቡኢም፥ በነብላት፥ 35 በሎድ፥ በኣውኖ፥ በጌሐራሲም ተቀመጡ። 36 ከሌዋውያንም ተከፍለው በይሁዳና በብንያም ነበሩ። |