ዘሌዋውያን 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ናዳብና አብዩድ በደል 1 የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ በየራሳቸው ጥናውን ወስደው እሳት አደረጉበት፤ በላዩም ዕጣን ጨመሩበት፤ በእግዚአብሔርም ፊት እግዚአብሔር ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ። 2 እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥቶ በላቸው፤ በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ። 3 ሙሴም አሮንን፥ “እግዚአብሔር፦ ወደ እኔ በሚቀርቡ እመሰገናለሁ፤ በሕዝቡም ሁሉ ፊት እከብራለሁ ብሎ የተናገረው ይህ ነው” አለው፤ አሮንም ደነገጠ። 4 ሙሴም የአሮንን አጎት የአዚሔልን ልጆች ሚሳዴንና ኤልሳፍንን ጠርቶ፥ “ሂዱ፤ ወንድሞቻቸሁን ከመቅደሱ ፊት አንሥታችሁ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዱአቸው” አላቸው። 5 እነርሱም ገብተው አነሡአቸው፤ ሙሴም እንዳለ በልብሳቸው ከሰፈር ወደ ውጭ ወሰዱአቸው። 6 ሙሴም አሮንን፥ ልጆቹንም አልዓዛርንና ኢታምርን፥ “እንዳትሞቱ፥ በማኅበሩም ላይ ሁሉ ቍጣ እንዳይወርድ ራሳችሁን አትንጩ፤ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ እግዚአብሔር ስላቃጠላቸው ማቃጠል ግን ወንድሞቻችሁ የእስራኤል ቤት ሁሉ ያልቅሱ። 7 የእግዚአብሔር የቅብዐት ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከምስክሩ ድንኳን ደጃፍ አትውጡ” አላቸው። ሙሴም እንዳዘዛቸው አደረጉ። ለአሮንና ለልጆቹ የተሠሩ ሕጎች 8 እግዚአብሔርም አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 9 “እንዳትሞቱ ወደ ምስክሩ ድንኳን ስትገቡ ወይም ወደ መሠዊያው ስትቀርቡ አንተና ልጆችህ የወይን ጠጅና የሚያሰክርን ነገር ሁሉ አትጠጡ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዐት ይሆናል፤ 10 በተቀደሰውና በአልተቀደሰው፥ በርኩሱና በንጹሑም መካከል ትለያላችሁ፤ 11 እግዚአብሔርም በሙሴ እጅ የነገራቸውን ሥርዐት ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ታስተምራቸዋለህ።” 12 ሙሴም አሮንን፥ የተረፉለትን ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን አላቸው፥ “ቅዱሰ ቅዱሳን ነውና ለእግዚአብሔር ከሆነው ከእሳት ቍርባን የቀረውን የስንዴውን ቍርባን ውሰዱ፤ ቂጣም አድርጋችሁ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት፤ 13 እግዚአብሔርም እንዲህ አዝዞኛልና፥ ለእግዚአብሔር ከሆነው ከእሳት ቍርባን ለአንተም፥ ለልጆችህም የተሰጠ ሥርዐት ነውና በቅዱስ ስፍራ ትበሉታላችሁ። 14 እነዚህም ከእስራኤል ልጆች ከደኅንነት መሥዋዕቶች ለአንተና ለልጆችህ ሥርዐት እንዲሆኑ ስለ ተሰጡ፥ የመሥዋዕቱን ፍርምባና ወርች አንተ፥ ከአንተ ጋርም ልጆችህ፥ ቤተሰብህም ተለይቶ በንጹሕ ስፍራ ትበላላችሁ። 15 የመሥዋዕቱን ወርችና ፍርምባ በእግዚአብሔር ፊት ከሚቀርበው መሥዋዕት የእሳት ቍርባን ከሆነው ስብ ጋር ያመጣሉ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ለአንተ፥ ከአንተ ጋርም ለወንዶችና ሴቶች ልጆችህ የዘለዓለም ሥርዐት ይሆናል።” 16 ሙሴም የኀጢአቱን መሥዋዕት ፍየል እጅግ ፈለገው፤ በፈለገውም ጊዜ እነሆ ተቃጥሎ ነበር፤ ሙሴም የቀሩትን የአሮንን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን ተቈጣቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ 17 “ቅዱሰ ቅዱሳን ነውና፥ የሕዝቡንም ኀጢአት እንድትሸከሙ፥ በእግዚአብሔርም ፊት እንድታስተሰርዩላቸው ይህን ትበሉ ዘንድ ለእናንተ ሰጥቶታልና ስለ ምን የኀጢአትን መሥዋዕት በቅዱሱ ስፍራ አልበላችሁም? 18 እነሆ፥ ደሙን ወደ መቅደስ ውስጥ አላገባችሁትም፤ እኔ እንደታዘዝሁ በቅዱስ ስፍራ ውስጥ ትበሉት ዘንድ ይገባችሁ ነበር።” 19 አሮንም ሙሴን ተናገረው እንዲህም አለው፥ “እነሆ፥ ዛሬ የኀጢአታቸውን መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕታቸውን በእግዚአብሔር ፊት በለዩ ጊዜ፥ ይህች አገኘችኝ፤ ዛሬም የኀጢአቱን መሥዋዕት እበላ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት መልካም አይደለም።” 20 ሙሴም ሰማ፤ ደስም አለው። |