Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa

መጽሐፈ ጥበብ 13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የአምልኮ ጣኦት ውግዘት፦ አምልኮተ ተፈጥሮ

1 እግዚአብሔርን የማያውቁ ሁሉ፥ በእውነት በባሕርያቸው ከንቱ ናቸው፤ ከሚታዩት መልካም ነገሮች፥ እርሱ የሆነውን ወደ ማወቅ አልደረሱም፤ አልያም የእጁን ሥራዎች በመመልከት፥ ሠሪውን ማስተዋል አልቻሉም።

2 ነገር ግን እሳት፥ ነፋስ ወይም ፈጣን አየር፥ ከዋክብት፥ ማዕበል ወይም የሰማይ ብርሃናትን ዓለምን ያስተዳድራሉ ብለው እንደ አማልክት ያመልኳቸው ነበር።

3 ውበታቸው የሚያማልለውን ሁሉ እንደ አማልክት ቆጠሯቸው፤ እነርሱን የፈጠረና የውበት ምንጭ የሆነው ጌታ የእነዚህ ጌታ ከእነርሱ ምን ያህል የላቀ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ አድርግ።

4 በኃይላቸውና በጉልበታቸውም ተማርከው ከሆነ፥ እነርሱን የፈጠረው ደግሞ ምን ያህል ኃያል እንደሆነ ይግባቸው፤

5 የፍጡራኑን ታላቅነትና ውበት በመመልከት፥ በንጽጽር ፈጣሪያቸው ከእነርሱ ምን ያህል የላቀ እንደሆነ ልንገምት እንችላለን።

6 ምናልባት ከመንገድ የወጡት አምላክን ፍለጋ እርሱንም ለማግኘት ካላቸው ጉጉት ሊሆን ይችላልና፥ እነኚህ ሰዎች ብዙ ሊወቀሱ አይገባም፤

7 በሥራዎቹ መሀል በፍለጋ ይደክማሉ፥ ከሚታዩት ነገሮች ውበት የተነሣ በሚያዩአቸው ነገሮች ምርኮኛ ሆነው ይቀራሉ።

8 ያም ሆኖ ግን የሚያመካኙበት ነገር አይኖርም።

9 ዓለምን ለመመርመር የሚበቃ ዕውቀት ካገኙ፥ ፈጣሪዋን ለማግኘት እንደምን ተሣናቸው?


አምልኮተ ጣኦት

10 ተስፋቸውን በሙት ነገሮች ላይ የሚያደርጉ፥ ወርቅም ይሁን ብር፥ የእንስሳት ምስሎችን፥ ጥንት በሰው እጅ የተቀረጹ ዋጋ የሌላቸው ድንጊያዎችን የሚያመልኩ ሁሉ ምስኪኖች ናቸው።

11 እንጨት ጠራቢውን ተመልከቱ፥ ለሥራው የሚስማማውን ዛፍ ይጥላል፤ ቅርፊቱን ሁሉ በጥንቃቄ ይልጣል፤ በጥበብ ጠርቦና አስተካክሎም የቤት ውስጥ መገልገያ ያደርገዋል።

12 ሲሠራ የወዳደቀውንም ቁርጥራጭ እንጨት፥ ረኃቡን የሚያስታግሥበትን ምግብ ያበስልበታል።

13 ከዚህም የሚተርፍ ጐባጣና ጉጥ የበዛበት፥ ለምንም የማይሆን እንጨት ይኖራል፤ ጠራቢውም ይህን እንጨት በዕረፍት ጊዜው ይልገዋል፤ ከልምድ ባገኘው ችሎታ ያስተካክለዋል፤ በሰው ምስል ይቀርጸዋል፤

14 ምናልባትም የሚያስቀይም እንስሳ መልክ ይሰጠዋል፤ በጭቃ ይለቀልቀዋል፤ ቀይ ቀለም ይቀባዋል፤ ጉድፉን ሁሉ ያጠፋለታል።

15 ቀጥሎም ለእርሱ የሚስማማ ቤት ይሠራለታል፤ ወደ ግድግዳው ያሰጠጋዋል፥ በብረት ቸንክሮም ያቆመዋል።

16 ራሱን መጠበቅ እንደማይችል በመረዳት፥ ምስል በመሆኑ ረዳት እንደሚያሻው ያውቅልና፤ እንዳይወድቅ በጥንቃቄ ያቆመዋል።

17 ይህም ሆኖ ግን እርሱ ስለሃብቱ፥ ስለ ጋብቻው፥ ስለልጆቹ መጸለይ ቢፈልግ፥ ይህን በድን ነገር ጮኾ ሲለምን አያፍርም። ጤናን ከደካማው፥

18 ሕይወትን ከበድን፥ ችሮታን ከሰው ከማይውለው፥ ስለ ጉዞ በእግሩ እንኳ መጠቀም ከማይችል፥

19 ስለ ትርፍ፥ ስለ ወደ ፊት ተግባሩና ስለሙያ ትጋቱ ጥበብን ይሰጠው ዘንድ፥ እጆቹ ከቶውንም ሰርተው ከማያውቁት ይለምናል።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos