ሕዝቅኤል 8 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ርኩሰት በቤተ መቅደስ 1 በስድስተኛውም ዓመት፥ በስድስተኛው ወር፥ ከወሩም በአምስተኛው ቀን፥ በቤቴ ተቀምጬ ሳለሁ የይሁዳም ሽማግሌዎች በፊቴ ተቀምጠው ሳሉ፥ በዚያም የጌታ የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ወደቀች። 2 እኔም አየሁ፥ እነሆም ሰውን የሚመስል ነበረ፥ ወገቡ ከሚመስለው በታች እሳት፥ ከወገቡም በላይ እንደ ብርሃን የሚመስል፥ የሚያንጸባርቅ ነገር የሚመስል ነበረ። 3 እጅ የሚመስል ዘረጋና በራስ ጠጉሬ ወሰደኝ፥ መንፈስም በምድርና በሰማይ መካከል አነሣኝ፥ በእግዚአብሔርም ራእዮች ወደ ኢየሩሳሌም፥ ቅናትን የሚያነሣሣ የቅናት ጣዖት ወደሚገኝበት፥ ወደ ሰሜን ወደሚመለከተው፥ ወደ ውስጠኛው አደባባይ በር መግቢያ አመጣኝ። 4 እነሆ በዚያ በሜዳው እንዳየሁት ራእይ የሚመስል የእስራኤል አምላክ ክብር ነበረ። 5 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ዐይኖችህን ወደ ሰሜን መንገድ አንሣ። እኔም ዐይኖቼን ወደ ሰሜን መንገድ አነሣሁ፥ እነሆም በመሠዊያው በር በሰሜን በኩል፥ በመግቢያው የቅናቱ ጣዖት ነበረ። 6 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ ከመቅደሴ ሊያርቁኝ፥ የእስራኤል ቤት በዚህ የሚፈጽሙትን ታላቅ ርኩሰት ታያለህን? ደግሞም ተመልሰህ ከዚህ የበለጠ ታላቅ ርኩሰት ታያለህ። 7 ወደ አደባባዩ መግቢያም አመጣኝ፥ አየሁም፥ እነሆ በግንቡ ላይ ቀዳዳ ነበረ። 8 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ ግንቡን ቦርቡረው አለኝ፥ ግንቡንም በቦረቦርሁት ጊዜ እነሆ አንድ መግቢያ አገኘሁ። 9 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ግባ፥ በዚህ የሚያደርጉትንም ክፉውን ርኩሰት ተመልከት። 10 እኔም ገባሁና አየሁ፥ እነሆ የሁሉም ዓይነት የሚሳቡ ነገሮች፥ የርኩሳን እንስሶች ምስሎችና የእስራኤል ቤት ጣዖታት ሁሉ በግንቡ ዙሪያ ተስለው ነበር። 11 ከእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች ሰባ ሰዎች ቆመው ነበር፥ የሻፋን ልጅ ያአዛንያ በመካከላቸው ቆሞ ነበር፥ እያንዳንዱም በእጁ ጥናውን ይዞ ነበር፥ መልካም መዓዛ ያለው የዕጣኑም ጢስ ወደ ላይ ይወጣ ነበር። 12 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ የእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች እያንዳንዱ በስዕሉ ቤት በጨለማ የሚያደርጉትን አይተሃልን? እነርሱም፦ “ጌታ አያየንም፥ ጌታ ምድሪቱን ትቶአታል፥ ብለዋልና።” 13 ደግሞም “ተመልሰህ ከዚህ የበለጠ ታላቅ ርኩሰት ሲያደርጉ ታያለህ” አለኝ። 14 ወደ ሰሜንም ወደሚመለከተው ወደ እግዚአብሔር ቤት በር መግቢያ አመጣኝ እነሆ፥ ሴቶች ለታሙዝ እያለቀሱ በዚያ ተቀምጠው ነበር። 15 እርሱም፦ “የሰው ልጅ ሆይ፥ ይህን አይተሃልን? ደግሞ ተመልሰህ ከዚህ የበለጠ ርኩሰት ታያለህ” አለኝ። 16 ወደ ጌታ ቤት ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፥ እነሆ በጌታ መቅደስ መግቢያ፥ በመተላለፊያውና በመሠዊያው መካከል ሃያ አምስት ያህል ሰዎች ነበሩ፥ ጀርባቸው ወደ ጌታ መቅደስ ፊታቸውም ወደ ምሥራቅ ነበረ፥ እነርሱም ወደ ምሥራቅ ለፀሐይ ይሰግዱ ነበር። 17 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ ይህን አይተሃልን? በዚህ የሰሩትን ርኩሰት ሊያደርጉ ለይሁዳ ቤት ይህ ቀላል ነገር ነውን? ምድሪቱን በዓመፅ ሞልተዋታል፥ ሊያስቆጡኝም ተመልሰዋል፥ እነሆ ቅርንጫፉን ወደ አፍንጫቸው አቅርበዋል። 18 ስለዚህ እኔ ደግሞ በቁጣ እሠራለሁ፥ ዓይኔ አይራራም፥ አላዝንምም፥ ወደ ጆሮዬም በታላቅ ድምፅ ቢጮኹም አልሰማቸውም።” |