ሕዝቅኤል 11 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የክፉ አማካሪዎች ፍርድ 1 መንፈስም ወደ ላይ አነሣኝ፥ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው ወደ ጌታ ቤት ወደ ምሥራቁ በር አመጣኝ። እነሆም በበሩ መግቢያ ሀያ አምስት ሰዎች ነበሩ፥ በመካከላቸውም የሕዝቡን መሪዎች የዓዙርን ልጅ ያአዛንያንንና የበናያ ልጅ ፈላጥያንን አየሁ። 2 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ክፋትን የሚያቅዱና በዚህችም ከተማ ክፉ ምክርን የሚመክሩ ሰዎች ናቸው። 3 እነርሱም፦ ቤቶች የሚሰሩበት ጊዜ ቅርብ አይደለምን? ይህች ከተማ ድስት ናት፥ እኛም ሥጋ ነን ብለዋል። 4 ስለዚህ ትንቢት ተናገርባቸው፥ የሰው ልጅ ሆይ ትንቢት ተናገር። 5 የጌታም መንፈስ ወደቀብኝ እንዲህም አለኝ፦ ጌታ እንዲህ ይላል ብለህ ተናገር፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ይህን ነገር ተናግራችኋል፥ እኔ የልባችሁን ሐሳብ አውቃለሁና። 6 በዚህች ከተማ ውስጥ የገደላችኋቸውን አብዝታችኋል፥ ጎዳናዎችዋንም በተገደሉት ሞልታችኋል። 7 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመካከልዋ ያኖራችኋቸው የተገደሉት እነርሱ ሥጋው ናቸው፥ ድስቱ ይህች ከተማ ናት፥ እናንተን ግን ከመካከልዋ አወጣችኋለሁ። 8 ሰይፍን ፈርታችኋል፥ እኔም ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 9 ከመካከልዋ አወጣችኋለሁ፥ በባዕዳንም እጅ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፥ በላያችሁም ላይ ፍርድ አመጣባችኋለሁ። 10 በሰይፍ ትወድቃላችሁ፥ በእስራኤልም ድንበር እፈርድባችኋለሁ፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። 11 ይህች ከተማ ድስት አትሆንላችሁም፥ እናንተም በመካከልዋ ሥጋ አትሆኑም፥ እኔም በእስራኤል ድንበር እፈርድባችኋለሁ። 12 እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፤ በትእዛዜ አልሄዳችሁምና፥ ሕጌንም አልፈጸማችሁምና፥ ነገር ግን በዙሪያችሁ እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ሕግ አድርጋችኋል። 13 ትንቢት እየተናገርሁ ሳለሁ የበናያስ ልጅ ፈላጥያ ሞተ፥ እኔም በግምባሬ ተደፍቼ በታላቅ ድምፅ ጮኽሁ እንዲህም አልሁ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ወዮ! የእስራኤልን ትሩፍ ፈጽመህ ታጠፋለህን? እግዚአብሔር እስራኤልን ያድሳል 14 የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 15 የሰው ልጅ ሆይ፥ ወንድሞችህ፥ ዘመዶችህ፥ የእስራኤልም ቤት ሁሉ፥ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሁሉ፥ “ከጌታ ራቁ፥ ምድሪቱ ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች” ብለዋል። 16 ስለዚህ እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በአሕዛብ መካከል አርቄ ብወስዳቸውም፥ በአገሮች መካከል ብበትናቸውም፥ በሄዱባቸው አገሮች በዚያ ትንሽ መቅደስ እሆናቸዋለሁ። 17 ስለዚህ እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከሕዝቦች መካከል እሰበስባችኋለሁ፥ ከተበተናችሁባቸው አገሮችም እሰበስባችኋለሁ፥ የእስራኤልንም ምድር ለእናንተ እሰጣችኋለሁ። 18 ወደዚያም ይመጣሉ፥ ጸያፉን ነገር ሁሉና ርኩሱን ነገር ሁሉ ከእርሷ ያወጣሉ። 19 አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ፥ አዲስ መንፈስም በውስጣቸው አኖራለሁ፥ ከሥጋቸውም የድንጋዩን ልብ አወጣለሁ፥ የሥጋንም ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ 20 ይህም በትእዛዜ እንዲሄዱ፥ ፍርዴንም እንዲጠብቁና እንዲፈጽሙ ነው፤ ስለዚህ እነርሱ ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 21 ልባቸው ወደ ጸያፍና ርኩስ ነገራቸው የሚከተል ግን መንገዳቸውን በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 22 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፥ መንኰራኵሮችም በአጠገባቸው ነበሩ፥ የእስራኤልም አምላክ ክብር በላያቸው ላይ ነበረ። 23 የጌታም ክብር ከከተማይቱ መካከል ተነሥቶ በከተማይቱ በምሥራቅ በኩል ባለው ተራራ ላይ ቆመ። 24 መንፈስም አነሣኝ፥ በእግዚአብሔርም መንፈስ በራእይ ወደ ከላውዴዎን ወደ ምርኮኞቹ አመጣኝ። ያየሁትም ራእይ ከእኔ ተለየ። 25 ጌታ ያሳየኝን ነገር ሁሉ ለምርኮኞቹ ተናገርሁ። |