የበለስ ፍሬ የተሞሉ ሁለት ቅርጫቶች1 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን፥ የይሁዳንም አለቆች፥ ብልሃተኞችንና እስረኞችን፥ ጓደኞቻቸውንም ከኢየሩሳሌም ማርኮ ወደ ባቢሎን ከአፈለሳቸው በኋላ፥ እነሆ እግዚአብሔር በእግዚአብሔር መቅደስ ፊት የተቀመጡ ሁለት የበለስ ቅርጫቶችን አሳየኝ። 2 በአንደኛዪቱ ቅርጫት አስቀድሞ እንደ ደረሰ በለስ የሚመስል እጅግ መልካም በለስ ነበረባት፤ በሁለተኛዪቱም ቅርጫት ከክፋቱ የተነሣ ይበላ ዘንድ የማይቻል እጅግ ክፉ በለስ ነበረባት። 3 እግዚአብሔርም፥ “ኤርምያስ ሆይ! የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ። እኔም፥ “በለስን አያለሁ፤ እጅግ መልካም የሆነ መልካም በለስ፥ ከክፋቱም የተነሣ ይበላ ዘንድ የማይቻል እጅግ ክፉ የሆነ ክፉ በለስ ነው” አልሁ። 4 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 5 “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፥ እንዲሁ ከዚህ ስፍራ ወደ ከለዳውያን ምድር የሰደድሁትን የይሁዳን ምርኮ ለበጎነት እመለከተዋለሁ። 6 ዐይኔንም ለበጎነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ ወደዚህችም ምድር ለመልካም እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም። 7 እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹምም ልባቸው ወደ እኔ ይመለሳሉና ሕዝቤ ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።” 8 እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፥ “ከክፋቱ የተነሣ ይበላ ዘንድ እንደማይቻል እንደ ክፉው በለስ፥ እንዲሁ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን፤ አለቆቹንም፥ በዚች ሀገር የሚቀሩትንም የኢየሩሳሌምን ቅሬታ፥ በግብጽም ሀገር የሚቀመጡትን እንዲሁ አደርጋቸዋለሁ። 9 በማሳድዳቸውም ስፍራ ሁሉ ለስድብና ለምሳሌ፥ ለጥላቻና ለርግማን ይሆኑ ዘንድ በምድር መንግሥታት ሁሉ እንዲበተኑ አደርጋለሁ። 10 ለእነርሱ፥ ለዘራቸውና ለአባቶቻቸውም ከሰጠኋቸው ምድር እስኪጠፉ ድረስ በመካከላቸው ሰይፍንና ራብን ቸነፈርንም እሰድዳለሁ።” |