የምድሪቱ ድንበር1 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2 “የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ ርስት እንዲሆናችሁ በዕጣ የምትደርሳችሁ ምድር፥ በተከለለው ድንበርዋ የከነዓን ምድር ይህች ናት፤ 3 የደቡቡ ወገን ከጺን ምድረ በዳ ተነሥቶ የኤዶምያስን ዳርቻ እያዋሰነ የሚያልፈው ይሆናል፤ የደቡቡም ድንበራችሁ ከጨው ባሕር ዳር በምሥራቅ በኩል ይጀምራል፤ 4 ድንበራችሁም በአቅረቢም ዐቀበት በደቡብ በኩል ይዞራል ወደ ጺንም ይሻገራል፤ በቃዴስ በርኔ በደቡብ በኩል ያለው መጨረሻው ይሆናል፤ ወደ ሐጸርአዳር ይሄዳል ወደ ዓጽሞንም ያልፋል፤ 5 ድንበሩም ከዓጽሞን ወደ ግብጽ ወንዝ ይዞራል፥ ባሕሩም ማብቂያው ይሆናል። 6 “ለምዕራብም ድንበር ታላቁ ባሕርና ዳርቻው ድንበራችሁ ይሆናል፤ ይህ የምዕራብ ድንበራችሁ ይሆናል። 7 “የሰሜንም ድንበራችሁ ይህ ይሆናል፤ ከታላቁ ባሕር ወደ ሖር ተራራ የወሰን ምልክት ታደርጋላችሁ። 8 ከሖርም ተራራ ወደ ሐማት መግቢያ የወሰን ምልክት ታደርጋላችሁ የድንበራችሁም መጨረሻ በጽዳድ ይሆናል፤ 9 ድንበሩም ወደ ዚፍሮን ይዘረጋል መጨረሻውም ሐጸርዔናን ይሆናል፤ ይህ የሰሜን ድንበራችሁ ይሆናል። 10 “የምሥራቁም ድንበራችሁን ከሐጸርዔናን ወደ ሴፋማ የወሰን ምልክት ታደርጋላችሁ፤ 11 ድንበሩም ከሴፋማ በዐይን ምሥራቅ ወዳለው ወደ ሪብላ ይወርዳል፤ እስከ ኪኔሬት የባሕር ወሽመጥ በምሥራቅ በኩል ይደርሳል፤ 12 ድንበሩም ወደ ዮርዳኖስ ይወርዳል፥ መጨረሻውም በጨው ባሕር ይሆናል። ምድራችሁ እንደ ድንበርዋ በዙሪያዋ ይህች ናት።” 13 ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “ጌታ ለዘጠኝ ነገድ ተኩል እንዲሰጥ ያዘዘው በዕጣ የምትወርሱአት ምድር ይህች ናት፤ 14 የሮቤልም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የጋድም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን ወርሰዋል። 15 እነዚህ ሁለቱ ነገድና የአንዱ ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን በዮርዳኖስ ማዶ በኢያሪኮ አንጻር በስተ ምሥራቅ፥ በፀሐይ መውጫ በኩል ወረሱ።” የእስራኤል ነገድ አለቆች16 ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 17 “ምድሪቱን ርስት አድርገው የሚከፋፍሉላችሁ ሰዎች ስማቸው ይህ ነው፤ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ። 18 ምድሪቱንም ርስት አድርገው ለመከፋፈል ከየነገዱ አንድ አንድ አለቃ ትወስዳላችሁ። 19 የሰዎቹም ስም ይህ ነው፤ ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፥ 20 ከስምዖን ልጆች ነገድ የዓሚሁድ ልጅ ሰላሚኤል፥ 21 ከብንያም ነገድ የኪስሎን ልጅ ኤልዳድ፥ 22 ከዳን ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የዮግሊ ልጅ ቡቂ፥ 23 ከዮሴፍም ልጆች ከምናሴ ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሱፊድ ልጅ አኒኤል፥ 24 ከኤፍሬም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሺፍጣን ልጅ ቀሙኤል፥ 25 ከዛብሎን ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የፈርናክ ልጅ ኤሊሳፈን፥ 26 ከይሳኮር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሖዛ ልጅ ፈልጢኤል፥ 27 ከአሴር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሴሌሚ ልጅ አሒሁድ፥ 28 ከንፍታሌም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ፈዳሄል። 29 ጌታ በከነዓን ምድር ለእስራኤል ልጆች ርስታቸውን እንዲያከፋፍሉ ያዘዛቸው እነዚህ ናቸው።” |