ዳዊት የሳኦልን ሕይወት ማትረፉ1 ዳዊትም ከዚያ ወደ ላይ ወጥቶ በዔንገዲ ምሽጎች ተቀመጠ። 2 ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ከተመለሰ በኋላ፥ “እነሆ፥ ዳዊት በዔንገዲ ምድረ በዳ አለ” ብለው ነገሩት። 3 ስለዚህ ሳኦል ከመላው እስራኤል የተመረጡ ሦስት ሺህ ሰዎችን ይዞ ዳዊትንና ሰዎቹን ለመፈለግ “የሜዳ ፍየሎች ዓለት” ወደ ተባለው ቦታ አቅራቢያ ሄደ። 4 ሳኦልም በመንገድ ዳር ወዳለው ወደ አንድ የበጎች ማደሪያ በደረሰ ጊዜ፥ ዋሻ አግኝቶ ወገቡን ሊሞክር ወደዚያ ገባ። ዳዊትና ሰዎቹም ከዋሻው በውስጠኛው ቦታ ተቀምጠው ነበር። 5 የዳዊት ሰዎችም ዳዊትን፥ “ጌታ፥ ‘የወደድኸውን ታደርግበት ዘንድ ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ’ ብሎ ለአንተ የተናገረው ቀን ዛሬ ነው” አሉት። ዳዊትም በልቡ እየተሳበ ሄዶ የሳኦልን ልብስ ጫፍ ማንም ሳያውቅ ቆርጦ ወሰደ። 6 ዳዊት የሳኦልን ልብስ ጫፍ በመቁረጡ ልቡ በኀዘን ተመታ። 7 ለሰዎቹም፥ “ጌታ በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ከማድረግና ጌታ የቀባው ስለ ሆነም እጄን በእርሱ ላይ ከማንሣት ጌታ ይጠብቀኝ” አላቸው። 8 ዳዊት ሰዎቹን በዚህ ቃል ከለከላቸው፤ በሳኦል ላይ አደጋ እንዲያደርሱበትም አልፈቀደላቸውም። ሳኦልም ከዋሻው ወጥቶ ሄደ። 9 ከዚያም ዳዊት ከዋሻው ወጥቶ ሳኦልን፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ!” ብሎ ጠራው። ሳኦልም ወደ ኋላው ዞር ባለ ጊዜ፥ ዳዊት ወደ መሬት ጐንበስ ብሎ እጅ ሲነሣው ተመለከተ፤ 10 ዳዊትም ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “ሰዎች፥ ‘እነሆ፤ ዳዊት ክፉ ነገር ሊያደርግብህ ይፈልጋል’ ሲሉ ለምን ትቀበላቸዋለህ? 11 በዛሬው ዕለት በዋሻው ውስጥ ጌታ አንተን እንዴት አድርጎ በእጄ ላይ እንደጣለህ እነሆ በገዛ ዓይንህ አይተሃል፤ አንዳንዶች እንድገድልህ ገፋፍተውኝ ነበር፤ እኔ ግን፥ ‘ጌታ በቀባው በጌታዬ ላይ እጄን አላነሣም’ በማለት ራራሁልህ። 12 አባቴ ሆይ፤ የልብስህ ቁራጭ ይኸው በእጄ ላይ ተመልከተው! የልብስህን ጫፍ ቆረጥሁ እንጂ አንተን አልገደልኩህም። አሁንም ክፋት ወይም ዐመፅ አለመፈጸሜን ዕወቅልኝ፤ ተረዳልኝም፤ እኔ ክፉ አልሠራሁብህም፤ አንተ ግን ሕይወቴን ለማጥፋት እያሳደድኸኝ ነው። 13 ጌታ በአንተና በእኔ መካከል ይፍረድ። ክፉ ስላደረግህብኝ ጌታ ይበቀልህ እንጂ እጄንስ በአንተ ላይ አላነሳም፤ 14 ጥንት፥ ‘ክፋት ክፋትን ይወልዳል’ እንደተባለ፤ አሁንም እጄ በአንተ ላይ አትሆንም። 15 የእስራኤል ንጉሥ የወጣው በማን ላይ ነው? አንተስ የምታሳድደው ማንን ነው? የሞተ ውሻን? ወይስ ቁንጫ? 16 አሁንም ጌታ ዳኛ ሆኖ በመካከላችን ይፍረድ፤ ጉዳዬን ተመልክቶ እርሱው ይሟገትልኝ፤ እኔንም ከእጅህ ነጻ ያውጣኝ።” 17 ዳዊት ይህን ተናግሮ ሲያበቃ ሳኦል፥ “ልጄ ዳዊት ሆይ፤ ይህ የአንተ ድምፅ ነውን?” ሲል ጠየቀው፤ ሳኦል ጮኾም አለቀሰ። 18 እንዲህም አለ፤ “ክፉ ሳደርግብህ፥ በጎ መልሰህልኛልና፥ አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ። 19 ያደረግህልኝን በጎ ነገር ይኸው ነግረኸኛል፤ ጌታ እኔን በእጅህ ቢጥልልህም አንተ ግን አልገደልኸኝም። 20 ለመሆኑ ጠላቱን አግኝቶ ጉዳት ሳያደርስበት የሚለቀው ማን ነው? ዛሬ ስላደረግህልኝ ቸርነት ጌታ ይመልስልህ። 21 እነሆ፤ አንተ በእርግጥ እንደምትነግሥና የእስራኤል መንግሥት በእጅህ እንደምትጸና ዐውቃለሁ። 22 ዘሮቼን እንዳታጠፋ ስሜንም ከአባቴ ቤት እንዳትደመስስ አሁን በጌታ ማልልኝ።” 23 ዳዊትም ለሳኦል ማለለት፤ ከዚያም ሳኦል ወደ ቤቱ ተመለሰ። ዳዊትና ሰዎቹ ግን ወደ አምባው ወጡ። |