La Biblia Online

Anuncios

Toda la Biblia A.T. N.T.


2 ሳሙኤል 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም
2 ሳሙኤል 3

1 በዚህ ዐይነት በሳኦል ቤተሰብና በዳዊት ቤተሰብ መካከል የሚካሄደው ጦርነት ለረጅም ጊዜ ቈየ፤ ሆኖም ዳዊት እየበረታ ሲሄድ የሳኦል ቤተሰብ እየተዳከመ ሄደ።

የዳዊት ልጆች

2 ዳዊት በኬብሮን ሳለ ስድስት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ እነርሱም በኲሩ የኢይዝራኤል ተወላጅ ከሆነችው ከአሒኖዓም የተወለደው አምኖን፥

3 ሁለተኛው የቀርሜሎስ ተወላጅ የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢጌል የተወለደው ኪልአብ፥ ሦስተኛው ታልማይ ተብሎ የሚጠራው የገሹር ንጉሥ ልጅ ከሆነችው ከማዕካ የተወለደው አቤሴሎም፥

4 አራተኛው ከሐጊት የተወለደው አዶኒያ፥ አምስተኛው ከአቢጣል የተወለደው ሸፋጥያ፥

5 ስድስተኛው ከሚስቱ ከዔግላ የተወለደው ዩትረዓም፥ እነዚህ ሁሉ በኬብሮን የተወለዱ ናቸው።

አበኔር ከዳዊት ጋር መተባበሩ

6 በሳኦል ቤተሰብና በዳዊት ቤተሰብ መካከል ጦርነቱ እየቀጠለ በሄደ መጠን አበኔር በሳኦል ቤተሰብ እየበረታ ሄደ።

7 ሳኦል የአያ ልጅ የሆነች ሪጽፋ የምትባል ቁባት ነበረችው፤ ኢያቡስቴ አበኔርን “ለምን ከአባቴ ቁባት ጋር ተገናኘህ” አለው።

8 የኢያቡስቴ ቃል አበኔርን በጣም አስቈጣው፤ እንዲህም አለ፦ “እኔ ወደ ይሁዳ ነገድ የዞርኩ የማልጠቅም ውሻ ነኝን? እኔ ለአባትህ ቤት፥ ለወንድሞቹና ለወዳጆቹ ታማኝነትን አሳይቼአለሁ፤ አንተንም ለዳዊት አሳልፌ አልሰጠሁህም፤ ታዲያ፥ አንተ ስለዚህች ሴት ትወቅሰኛለህን?

9-10 እግዚአብሔር መንግሥትን ከሳኦል ቤት ወሰደ የዳዊትን ዙፋን በእስራኤልና በይሁዳ ላይ ከሰሜን ከዳን ጀምሮ እስከ ደቡብ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ለመዘርጋት በመሐላ ቃል በገባለት መሠረት ባላስፈጽም በእኔ ላይ እግዚአብሔር ይፍረድ!”

11 ኢያቡስቴም እጅግ ፈርቶ ስለ ነበር፥ ለአበኔር አንድ ቃል እንኳ ሊመልስለት አልቻለም።

12 አበኔር በዚያን ጊዜ በኬብሮን ወደነበረው ወደ ዳዊት መልእክተኞች ልኮ “የዚህች ምድር ገዢ የሚሆን ማነው? እንግዲህ ከእኔ ጋር ስምምነት አድርግ፤ እኔም መላው እስራኤል በአንተ ቊጥጥር ሥር እንዲሆን ለማድረግ እረዳሃለሁ” አለው።

13 ዳዊትም “መልካም ነው! ከአንተ ጋር ስምምነት አደርጋለሁ፤ ነገር ግን አንተ በቅድሚያ የምትፈጽምልኝ ነገር አለ፤ ይኸውም ወደ እኔ በምትመጣበት ጊዜ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን ይዘህ ካልመጣህ መገናኘት አንችልም” አለው።

14 እንዲሁም ዳዊት ወደ ኢያቡስቴ መልእክተኞች ልኮ እንዲህ አለው፤ “ሚስቴን ሜልኮልን መልስልኝ፤ እኔ እርስዋን ለማግባት የአንድ መቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ማጫ ጥያለሁ” አለው።

15 ስለዚህም ኢያቡስቴ መልእክተኛ በመላክ ሜልኮል የላዊሽ ልጅ ከሆነው ከባልዋ ከፓልጢኤል ልጅ አስወሰዳት፤

16 ባልዋ ፓልጢኤልም እያለቀሰ እስከ ባሑሪም ከተማ ድረስ ተከተላት፤ ነገር ግን አበኔር “ወደ ቤትህ ተመለስ” ባለው ጊዜ ተመለሰ።

17 አበኔር ወደ እስራኤል መሪዎች ሄዶ እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊት የእናንተ ንጉሥ እንዲሆን ለብዙ ጊዜ ተመኝታችሁ ነበር፤

18 እነሆ፥ አሁን አድርጉ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ‘በአገልጋዬ በዳዊት አማካይነት ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያንና ከሌሎቹም ጠላቶቻቸው እጅ በመታደግ አድናለሁ’ ሲል ተናግሮ እንደ ነበር አስታውሱ።”

19 አበኔር ለብንያም ነገድ ሕዝብም ይህንኑ ተናገረ፤ ከዚያም በኋላ የብንያምና የእስራኤል ሕዝብ ለማድረግ የተስማሙበትን ጉዳይ ለዳዊት ለመንገር ወደ ኬብሮን ሄደ።

20 አበኔር ኻያ ሰዎችን አስከትሎ ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን በመጣ ጊዜ ዳዊት ግብዣ አደረገላቸው፤

21 አበኔርም ዳዊትን “ከአንተ ጋር እንዲነጋገሩና እንዲዋዋሉ አንተም ልብህ በተመኘው ሁሉ ላይ እንድትነግሥ ለማድረግ ወደ እስራኤላውያን ልሂድ” አለው። በዚህም ዐይነት ዳዊት አበኔርን በሰላም አሰናበተው።

የአበኔር መገደል

22 ጥቂት ዘግየት ብሎ ኢዮአብና ሌሎች የዳዊት ወታደሮች ብዙ ምርኮ ካገኙበት ዘመቻ ተመለሱ፤ ይሁን እንጂ አበኔር በዚያን ጊዜ ዳዊት በሰላም አሰናብቶት ሄዶ ስለ ነበር በኬብሮን አልነበረም፤

23 ኢዮአብና ተከታዮቹ በደረሱም ጊዜ የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሥ ዳዊት መጥቶ ንጉሡ አበኔርን በሰላም እንዳሰናበተው ለኢዮአብ ነገሩት።

24 ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቀርቦ እንዲህ አለው፦ “ይህ ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው? አበኔር ወደ አንተ መጥቶ ሳለ እንዲሁ እንዲሄድ ያሰናበትከው ስለምንድን ነው?

25 የኔርን ልጅ አበኔርን ታውቀዋለህ፤ እርሱ የመጣው አንተን አታሎ የምትወጣበትንና የምትገባበትን ለማየትና ምን እንደምታደርግ ለመሰለል ነው።”

26 ኢዮአብ ከዳዊት ፊት ወጥቶ ከሄደ በኋላ አበኔርን ያመጡት ዘንድ መልእክተኞች ላከ፤ እነርሱም ከሲራ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ መልሰው አመጡለት፤ ዳዊት ግን ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም።

27 አበኔር ወደ ኬብሮን በደረሰ ጊዜ ኢዮአብ በግል ሊያነጋግረው የፈለገ በመምሰል ወደ ቅጽሩ በር ገለል አድርጎ ወሰደው፤ እዚያም ሆዱን ወግቶ ገደለው፤ ኢዮአብ ይህን ያደረገበት ምክንያት አበኔር ቀደም ብሎ ወንድሙን ዐሣሄልን ስለ ገደለበት ለመበቀል ነው።

28 ዳዊትም የአበኔርን መገደል በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “እኔና በንጉሣዊ ግዛቴ ውስጥ ያለው ሕዝብ ስለ አበኔር መገደል ከደሙ ንጹሓን መሆናችንን እግዚአብሔር ያውቃል።

29 ስለዚህም ቅጣቱ በኢዮአብና በቤተሰቡ ላይ ይውረድ! በዘመናት ሁሉ ከቤተሰቡ የአባለ ዘር ወይም የሥጋ ደዌ ያለበት ሰው አይጥፋ! እንዲሁም አካለ ስንኩል የሆነ ሰው፥ በጦር ሜዳ የሚሞት ወይም የሚበላው አጥቶ የሚራብ ሰው አይታጣ!”

30 በዚህ ዐይነት ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳይ ወንድማቸውን ዐሣሄልን በገባዖን በተደረገው ጦርነት ስለ ገደለ አበኔርን ገደሉት።

የአበኔር በድን መቀበር

31 ከዚህ በኋላ ዳዊት በሐዘን ልብሳቸውን ቀደው፥ ማቅ ለብሰው ለአበኔር እንዲያለቅሱ ኢዮአብንና የእርሱ ተከታዮች የሆኑትን ሰዎች አዘዘ፤ በቀብር ሥነ ሥርዓቱም ላይ ንጉሥ ዳዊት ራሱ አስክሬኑን ተከትሎ ሄደ፤

32 አበኔር በኬብሮን ተቀበረ፤ በመቃብሩም ላይ ንጉሡ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ እርሱን በማየት በመረረ ሁኔታ አለቀሱ፤

33 ዳዊትም ለአበኔር ሐዘኑን በቅኔ ሲገልጥ እንዲህ አለ፦ “አበኔር እንደ ሞኝ ሰው ይሙትን?

34 እጆችህ አልታሰሩም፤ እግሮችህ አልታበቱም፤ ታዲያ፥ በዚህ ሁኔታ ሳለ በወንጀለኞች እጅ እንደሚወድቅ ሰው እንዴት ተገደልክ!” ሕዝቡም ሁሉ ስለ እርሱ እንደገና አለቀሱ።

35 ሰዎችም ቀኑን ሙሉ ዳዊት እህል ይቀምስ ዘንድ ለማግባባት ሞከሩ፤ እርሱ ግን “የዛሬይቱ ጀንበር ሳትጠልቅ እህል ብቀምስ እግዚአብሔር ይቅጣኝ!” ሲል ማለ።

36 ሕዝቡም ሁሉ ይህን ነገር ተመልክተው ደስ አላቸው፤ በእርግጥም ንጉሡ ያደረገው ነገር ሁሉ ሕዝቡን ደስ አሰኛቸው።

37 የዳዊት ሰዎችና መላው የእስራኤል ሕዝብ በአበኔር ሞት ንጉሥ ዳዊት ምንም ያልተባበረ መሆኑን ተገነዘቡ።

38 ንጉሡም ባለሟሎቹ ለሆኑት ባለሥልጣኖች እንዲህ አለ፤ “በዛሬው ቀን በእስራኤል ታላቅ መሪ እንደ ሞተ አታስተውሉምን?

39 ምንም እንኳ እኔ እግዚአብሔር መርጦ የሾመኝ ንጉሥ ብሆን ዛሬ ደካማነት ተሰምቶኛል፤ እነዚህ የጸሩያ ልጆች በእኔ ላይ እጅግ የበረቱ ዐመፀኞች ሆነውብኛል፤ እነዚህን ነፍሰ ገዳዮች እግዚአብሔር ራሱ የሚገባቸውን ቅጣት ይስጣቸው!”

Mostrar Biblia Interlineal

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia