Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ሳሙኤል 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ዳዊት የይሁዳ ንጉሥ መሆኑ

1 ከዚህ በኋላ ዳዊት ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንድዋ ልውጣን? ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም “አዎ ውጣ” አለው። ዳዊትም “ወደ የትኛይቱ ከተማ ልሂድ?” ሲል ጠየቀ። እግዚአብሔርም “ወደ ኬብሮን ከተማ ሂድ” አለው።

2 ስለዚህ ዳዊት ከሁለቱ ሚስቶቹ ጋር ወደ ኬብሮን ሄደ፤ እነርሱም የኢይዝራኤል ተወላጅ የሆነችው የአሒኖዓምና የቀርሜሎሳዊው የሟቹ የናባል ሚስት አቢጌል ነበሩ።

3 እንዲሁም ዳዊት ተከታዮቹን ከነቤተሰባቸው ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ በኬብሮን ዙሪያ ባሉትም ታናናሽ ከተሞች ተቀመጡ።

4 ከዚህ በኋላ የይሁዳ ሰዎች ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትንም ቀብተው የይሁዳ ንጉሥ አደረጉት። ዳዊት ገለዓዳውያን የሆኑ የያቤሽ ሰዎች ሳኦልን እንደ ቀበሩት በሰማ ጊዜ፥

5 ዳዊት ወደ ያቤሽ ገለዓድ ሰዎች መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አላቸው፦ “እርሱን በመቅበር ለጌታችሁ ለሳኦል ቸርነትን ስላሳያችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ።

6 ደግሞም እግዚአብሔር ቸርነቱንና ታማኝነቱን ይግለጥላችሁ፤ እናንተ ስለ ፈጸማችሁት መልካም ነገር እኔም ለእናንተ ወሮታችሁን እመልሳለሁ።

7 እንግዲህ ጠንክሩ! በርቱም! ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአል፤ የይሁዳ ሕዝብ እኔን ቀብቶ አንግሦኛል።”


ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ መንገሡ

8 የሳኦል ሠራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔር ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ ጋር የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር ወደ ማሕናይም ሸሽቶ ሄደ፤

9 በዚያም አበኔር ኢያቡስቴን በገለዓድ ግዛቶች፥ በአሴር፥ በኢይዝራኤል፥ በኤፍሬምና በብንያም ይኸውም በመላው እስራኤል ላይ እንዲነግሥ አደረገ።

10 እርሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበር፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። የይሁዳ ነገድ ግን ዳዊትን ተከተለ፤

11 ዳዊትም በኬብሮን ተቀምጦ በመላው ይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ተኩል ነገሠ።


በእስራኤልና በይሁዳ መካከል የተደረገው ጦርነት

12 አበኔርና የኢያቡስቴ ባለሟሎች ከማሕናይም ተነሥተው ወደ ገባዖን ከተማ መጡ፤

13 እናቱ ጸሩያ ተብላ የምትጠራው ኢዮአብና ሌሎቹም የዳዊት ባለሥልጣኖች ወጥተው በገባዖን ኲሬ ውሃ አጠገብ ተገናኙ፤ ሁሉም በቡድን ተከፋፍለው በኲሬው ውሃ ማዶ ለማዶ ተቀምጠው ነበር።

14 በዚህ ጊዜ አበኔር ኢዮአብን “ከእያንዳንዳችን ወገን ወጣቶችን መርጠን በጦር መሣሪያ ውጊያ በመግጠም ይወዳደሩ” አለው። ኢዮአብም “መልካም ነው” ሲል መለሰ።

15 ስለዚህም ከብንያም ወገን የኢያቡስቴ ተወካዮች የሚሆኑ ዐሥራ ሁለት ሰዎች ተመርጠው ከዳዊት ወገን ከተመረጡት ዐሥራ ሁለት ሰዎች ጋር ውጊያ ገጠሙ።

16 እያንዳንዱ ሰው የባለጋራውን ራስ ይዞ ሰይፉን በጐኑ ሻጠበት፤ በዚህ ዐይነት ኻያ አራቱም ሰዎች በአንድነት ወድቀው ሞቱ፤ ስለዚህም በገባዖን የሚገኘው ያ ስፍራ “የሰይፍ ምድር” ተብሎ ተጠራ።

17 በዚያም ቀን ከባድ ጦርነት ተደርጎ አበኔርና እስራኤላውያን በዳዊት ሰዎች ድል ተመቱ።

18 ኢዮአብ፥ አቢሳ፥ ዐሣሄል ተብለው የሚጠሩት ሦስቱም የጸሩያ ልጆች እዚያ ነበሩ፤ በሩጫ እንደ በረሓ ሚዳቋ ፈጣን የነበረው አሳሔል፥

19 አበኔርን አባሮ ለመያዝ በቀጥታ ወደ እርሱ ሮጠ፤

20 አበኔርም፥ ወደ ኋላው መለስ ብሎ “ዐሣሄል፥ አንተ ነህ?” አለ። ዐሣሄልም “አዎ እኔ ነኝ” ሲል መለሰለት።

21 አበኔርም “እኔን ማሳደድ ተው! ይልቅስ ከወታደሮቹ አንዱን በማሳደድ የያዘውን ምርኮ ውሰድ” አለው፤ ዐሣሄል ግን እርሱን ማሳደዱን ቀጠለ፤

22 እንደገናም አበኔር “እኔን ማሳደድህን ተው! ለምን እንድገድልህ ትገፋፋኛለህ? አንተንስ ብገድል የወንድምህን የኢዮአብን ፊት እንዴት ማየት እችላለሁ?” አለው።

23 ዐሣሄል ግን አሁንም ማሳደዱን ሊተው አልፈቀደም፤ ስለዚህ አበኔር ጦሩን ወደ ኋላው ወርውሮ ሆዱ ላይ ሲሽጥበት ጫፉ ዘልቆ በጀርባው ወጣ፤ ዐሣሄልም መሬት ላይ ወድቆ ሞተ፤ ሬሳው በተጋደመበት ስፍራ የሚያልፍ ሰው ሁሉ በአጠገቡ ቆሞ ይመለከተው ነበር።

24 ኢዮአብና አቢሳ ግን አበኔርን አሳደዱት፤ ፀሐይ በጠለቀች ጊዜም ከጊያሕ በስተ ምሥራቅ፥ ወደ ገባዖን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ወዳለው ወደ አማ ኮረብታ ደረሱ።

25 የብንያም ነገድ ሰዎች እንደገና ተሰብስበው ወደ አበኔር መጡ፤ በአንድ ኮረብታም ጫፍ ላይ ለጦርነት በመዘጋጀት ተሰለፉ።

26 አበኔርም፥ ኢዮአብን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ዘለዓለም ስንዋጋ እንኖራለንን? ፍጻሜውስ መራር መሆኑን አትገነዘብምን? ሰዎችህ እኛን ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ እንዲገቱ ትእዛዝ የማትሰጣቸው እስከ መቼ ነው?”

27 ኢዮአብም “አንተ ይህን ቃል ባትናገር ኖሮ የእኔ ሰዎች እስከ ነገ ጠዋት ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ እንደማይገቱ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ” ሲል መለሰለት።

28 ከዚህ በኋላ ኢዮአብ እምቢልታውን ነፋ፤ ሰዎችም ሁሉ ቆሙ፤ ከዚያ በኋላ እስራኤልን አላሳደዱም፤ ጦርነቱንም አልቀጠሉም።

29 አበኔርና ሰዎቹ ሌሊቱን ሁሉ በመጓዝ በዓራባ ሸለቆ በኩል ሄዱ፤ ዮርዳኖስንም ተሻግረው በመጓዝ ቢትሮንን ሁሉ ዓልፈው ወደ ማኅናይም መጡ።

30 ኢዮአብ አበኔርን ከማሳደድ በተመለሰ ጊዜ ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፤ በዚህ ጊዜ ከዳዊት ሰዎች መካከል ከዐሣሔል ሌላ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች መጒደላቸው ታወቀ።

31 የዳዊት ሰዎች የብንያም ነገድ ከሆኑት ከአበኔር ተከታዮች ሦስት መቶ ሥልሳ ሰዎችን ገደሉ።

32 ኢዮአብና ከእርሱ ጋር የነበሩት ተከታዮቹ የዐሣሄልን አስክሬን ወስደው በቤተልሔም በሚገኘው በቤተሰቡ መቃብር ውስጥ ቀበሩት፤ ሌሊቱንም ሁሉ ሲገሠግሡ አድረው ጎሕ ሲቀድ ኬብሮን ደረሱ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos