ኢሳይያስ 55:11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ነው፤ የምሻውን እስኪያደርግ ድረስ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም፤ መንገዴንና ትእዛዜን አከናውናለሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከአፌ የሚወጣ ቃል እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል፤ የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከእኔ አንደበት የሚወጣውም ቃል እንደዚሁ ነው። እርሱ የላክሁትን ጉዳይ ሳያከናውንና ተልእኮውን ሳይፈጽም ወደ እኔ አይመለስም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ከአፌ የሚወጣ ቃል እንዲሁ ይሆናል፥ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም። |
ቃሌ ከአፌ በጽድቅ ወጥታለች፤ አትመለስምም፤ ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ ምላስም ሁሉ በእግዚአብሔር ይምላል ብዬ በራሴ ምያለሁ።”
በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እናገራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች፤ የመከርሁትንም ሁሉ አደርጋለሁ እላለሁ።
እግዚአብሔር ከግርፋቱ ያነጻው ዘንድ ፈቀደ፤ ስለ ኀጢአት መሥዋዕትን ብታቀርቡ ሰውነታችሁ ረዥም ዕድሜ ያለውን ዘር ታያለች።
“ከእነርሱ ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር፤ “በአንተ ላይ ያለው መንፈሴ በአፍህም ውስጥ ያደረግሁት ቃሌ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ ከአፍህ፥ ከዘርህም አፍ፥ ከዘር ዘርህም አፍ አይጠፋም፥” ይላል እግዚአብሔር።
ሁለተኛም ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ምን ታያለህ?” እኔም፥ “የሚፈላ አፍላል አያለሁ፤ ፊቱም ወደ ሰሜን ወገን ነው” አልሁ።
በእርስዋም ላይ የተናገርሁትን ቃሌን ሁሉ፥ ኤርምያስ በአሕዛብ ሁሉ ላይ በትንቢት የተናገረውን በዚች መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ፥ በዚያች ምድር ላይ አመጣለሁ።
እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ እመጣለሁ፤ እኔም አደርገዋለሁ፤ አልተውም፤ አልራራም፤ አልጸጸትም፤ እንደ መንገድሽና እንደ ሥራሽም እፈርድብሻለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ስለዚህ የሰውን ደም እንደ አፈሰስሽ እኔ እፈርድብሻለሁ፤ እንደ ኀጢአትሽም ተበቅዬ አጠፋሻለሁ፤ ስምሽም ጐሰቈለ፥ ብዙ ኀዘንንም ታዝኛለሽ።”
ለባሪያዎቼስ ለነቢያት ያዘዝኋቸው ቃሎቼና ሥርዓቴ በአባቶቻችሁ ላይ አልደረሱምን? እነርሱም ተመልሰው፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በመንገዳችንና በሥራችን መጠን ያደርግብን ዘንድ እንዳሰበ እንዲሁ አድርጎብናል አሉ።
እግዚአብሔር እንደ ሰው የሚታለል አይደለም። እንደ ሰው ልጅም የሚዛትበት አይደለም፤ እርሱ ያለውን አያደርገውምን? አይናገረውምን? አይፈጽመውምን?
ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ግን አንዳች አይጠቅምም፤ ይህም እኔ የምነግራችሁ ቃል መንፈስ ነው፤ ሕይወትም ነው።
ትምህርቴንም እንደ ዝናም ተስፋ ታድርገው፤ ነገሬ እንደ ጠል ይውረድ፤ በእርሻም ላይ እንደ ዝናም፥ በሣርም ላይ እንደ ጤዛ።
ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።
ምድርም በእርስዋ የሚወርደውን ዝናም ከጠጣች፥ ያንጊዜ ስለ እርሱ ያረሱላትን መላካም ቡቃያ ታበቅላለች፤ ከእግዚአብሔር ዘንድም በረከትን ታገኛለች።