ሉቃስ 12:32 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም “እናንተ አነስተኛ መንጋ የሆናችሁ፤ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ መልካም ፈቃድ ነውና አትፍሩ፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) “አንተ ታናሽ መንጋ! መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “እናንተ እንደ ታናናሽ መንጋ የሆናችሁ ወገኖቼ አትፍሩ፤ የሰማይ አባታችሁ መንግሥትን ሊሰጣችሁ ፈቅዶአል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “አንተ ታናሽ መንጋ፥ አትፍራ፤ አባታችሁ መንግሥቱን ሊሰጣችሁ ወዶአልና። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። |
“እኔም፣ “ ‘የተመረጠችውን ምድር፣ የትኛውም ሕዝብ ያላገኘውን የተዋበች ርስት ልሰጥሽ፣ እንደ ወንዶች ልጆቼ ምንኛ በደስታ ልቍጠርሽ’ አልሁ፤ ‘አባቴ’ ብለሽ የምትጠሪኝ፣ እኔንም ከመከተል ዘወር የማትዪ መስሎኝ ነበር።
“በዚያ ጊዜ ንጉሡ በቀኙ በኩል ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፤ ‘እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ፤
በዚያ ጊዜ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አድርጎ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ፤ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፤ ይህ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኗልና።
ኢየሱስም፣ “የእኔ መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለም፤ ቢሆንማ ኖሮ አይሁድ እንዳይዙኝ አገልጋዮቼ በተከላከሉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም” አለው።
ለራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስ ቆጶሳት አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ።
ከእግዚአብሔር ጥበብ የተነሣ ዓለም በገዛ ጥበቧ እግዚአብሔርን ማወቅ ስለ ተሳናት፣ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ያድን ዘንድ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኗል።
ይህን እያሰብን አምላካችን ለጥሪው የበቃችሁ አድርጎ እንዲቈጥራችሁ፣ በጎ ለማድረግ ያላችሁን ምኞትና ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን ሁሉ በኀይሉ እንዲፈጽምላችሁ ዘወትር ስለ እናንተ እንጸልያለን።
ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርድ ቅን መሆኑን የሚያመለክት ነው፤ ከዚህም የተነሣ መከራን ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የበቃችሁ ሆናችሁ ትቈጠራላችሁ።
ስለዚህ ከቶ የማይናወጥ መንግሥት ስለምንቀበል እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደግሞም ደስ በሚያሠኘው መንገድ በአክብሮትና በፍርሀት እናምልከው፤
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጠጋ እንዲሆኑና እርሱን ለሚወድዱም ተስፋ የተሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን?
ከእንግዲህ ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤ ጌታ አምላክ ስለሚያበራላቸው የመብራት ወይም የፀሓይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ከዘላለም እስከ ዘላለምም ይነግሣሉ።