ኢዩኤል 2:31 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ፀሓይ ወደ ጨለማ፤ ጨረቃም ወደ ደም ትለወጣለች። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ታላቁና የሚያስፈራው የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ታላቁና አስፈሪው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ደም ትመስላለች፤ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ታላቋና ግልጥ የሆነችው የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል። |
በጽዮን መለከትን ንፉ፤ በቅዱሱ ተራራዬም የማስጠንቀቂያውን ድምፅ አሰሙ። በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ፤ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና፤ እርሱም በደጅ ነው።
በሰራዊቱ ፊት፣ እግዚአብሔር ያንጐደጕዳል፤ የሰራዊቱ ብዛት ስፍር ቍጥር የለውም፤ ትእዛዙንም የሚያደርግ እርሱ ኀያል ነው፤ የእግዚአብሔር ቀን ታላቅ፣ እጅግም የሚያስፈራ ነው፤ ማንስ ሊቋቋመው ይችላል?
ይህም የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው። የንጋት ብርሃን በተራሮች ላይ እንደሚወጣ፣ ኀያልና ብዙ ሰራዊት ይመጣል፤ ከጥንት እንዲህ ዐይነት ከቶ አልነበረም፤ በሚመጡትም ዘመናት እንዲህ ዐይነት ከቶ አይሆንም።
“እነሆ፤ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞች ሁሉና ክፉ አድራጊዎች በሙሉ ገለባ ይሆናሉ፤ ያ የሚመጣው ቀንም ያቃጥላቸዋል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “ሥርም ሆነ ቅርንጫፍ አያስቀርላቸውም።
“ወዲያውኑ ከእነዚያ ከመከራው ቀናት በኋላ፣ “ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፤ ጨረቃ ብርሃኗን ትከለክላለች፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናጋሉ።’
አራተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ የብርሃናቸው አንድ ሦስተኛ ይጨልም ዘንድ፣ የፀሓይ አንድ ሦስተኛ፣ የጨረቃም አንድ ሦስተኛ፣ የከዋክብትም አንድ ሦስተኛ ተመታ፤ የቀንም አንድ ሦስተኛ፣ የሌሊቱም አንድ ሦስተኛ ብርሃን እንዳይሰጥ ተከለከለ።