ሐጌ 2:6 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በቅርቡ፣ አንድ ጊዜ እንደ ገና ሰማያትንና ምድርን፣ ባሕሩንና የብሱን አናውጣለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላልና፦ እንደገና በቅርብ ጊዜ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስን አናውጣለሁ፤ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም የሠራዊት አምላክ እንዲህ ይላል፦ “በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደገና ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንና የብስን አናውጣለሁ፤ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ገና አንድ ጊዜ በቅርብ ዘመን እኔ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስንም አናውጣለሁ፣ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ገና አንድ ጊዜ በቅርብ ዘመን እኔ ሰማያትንና ምድርን ባሕርንና የብስንም አናውጣለሁ፥ |
እግዚአብሔር ምድርን ለማናወጥ በሚነሣበት ጊዜ፣ ሰዎች ከአስፈሪነቱ ከግርማውም የተነሣ፣ ወደ ዐለት ዋሻ፣ ወደ መሬትም ጕድጓድ ለመሸሸግ ይሮጣሉ።
የሰማይ ከዋክብት ሁሉ ይሟሽሻሉ፤ ሰማይ እንደ ብራና ይጠቀለላል፤ የከዋክብት ሰራዊት ሁሉ፣ ጠውልጎ እንደ ረገፈ የወይን ቅጠል፣ ደርቆም እንደ ወደቀ የበለስ ቅጠል ይሆናሉ።
የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የባቢሎን ሴት ልጅ በመረገጥ ላይ እንዳለ፣ የእህል መውቂያ ዐውድማ ናት፤ የመከር ወራቷም ፈጥኖ ይደርስባታል።”
የባሕር ዓሦች፣ የሰማይ ወፎች፣ የምድር አራዊት፣ በምድር ላይ የሚሳብ ፍጡር ሁሉ፣ እንዲሁም በምድር ላይ ያለ ሰው ሁሉ፣ በፊቴ ይንቀጠቀጣሉ፤ ተራሮች ይገለባበጣሉ፤ ገደሎች ይናዳሉ፤
እግዚአብሔር ከጽዮን ጮኾ ይናገራል፤ ከኢየሩሳሌም ያንጐደጕዳል፤ ሰማይና ምድርም ይናወጣሉ፤ እግዚአብሔር ግን ለሕዝቡ መሸሸጊያ፣ ለእስራኤልም ልጆች መጠጊያ ይሆናል።