ሐጌ 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምቃል የተገባው የአዲሱ ቤት ክብር 1 በሰባተኛው ወር፣ በሃያ አንደኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፤ 2 “ለይሁዳ ገዥ ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፣ ለሊቀ ካህናቱ ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱ፣ ከምርኮ ለተረፈውም ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ እንዲህም ብለህ ጠይቃቸው፤ 3 ‘ይህን ቤት በቀድሞ ክብሩ ሳለ ያየ ከመካከላችሁ ማን አለ? አሁንስ ምን መስሎ ይታያችኋል? ይህ በፊታችሁ ምንም እንዳይደለ የሚቈጠር አይደለምን?’ 4 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አሁን ግን ዘሩባቤል ሆይ፤ በርታ፤ የሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፤ በርታ፤ እናንተም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በርቱ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘እኔ ከእናንተ ጋራ ነኝና ሥሩ’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር፤ 5 ‘ከግብጽ በወጣችሁ ጊዜ የገባሁላችሁ ቃል ይህ ነው፤ መንፈሴም በመካከላችሁ ይሆናልና አትፍሩ።’ 6 “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በቅርቡ፣ አንድ ጊዜ እንደ ገና ሰማያትንና ምድርን፣ ባሕሩንና የብሱን አናውጣለሁ። 7 ሕዝቦችን ሁሉ አናውጣለሁ፤ የሕዝቦችም ሀብት ሁሉ ወደዚህ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 8 ‘ብሩ የእኔ ነው፤ ወርቁም የእኔ ነው’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ 9 ‘የዚህ የአሁኑ ቤት ክብር ከቀድሞው ቤት ክብር ይበልጣል’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ‘በዚህም ቦታ ሰላምን እሰጣለሁ’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” ተግሣጽና በረከት 10 ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ በዘጠነኛው ወር፣ በሃያ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፤ 11 “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሕጉ ምን እንደሚል ካህናቱን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፤ 12 አንድ ሰው የተቀደሰውን ሥጋ በልብሱ ዕጥፋት ቢይዝ፣ ያም ዕጥፋት እንጀራ ወይም ወጥ፣ የወይን ጠጅ ወይም ዘይት ወይም ሌላ ምግብ ቢነካ የተቀደሰ ይሆናልን?’ ” ካህናቱም፣ “የተቀደሰ አይሆንም” ብለው መለሱ። 13 ሐጌም፣ “ሬሳ በመንካቱ የረከሰ ሰው፣ ከእነዚህ አንዱን ቢነካ፣ የተነካው ነገር ይረክሳልን?” ሲል ጠየቀ። ካህናቱም፣ “አዎን፣ ይረክሳል” ሲሉ መለሱ። 14 ከዚያም ሐጌ እንዲህ አለ፤ “ ‘ይህ ሕዝብና ይህ ወገንም በፊቴ እንደዚሁ ነው’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘የእጃቸው ሥራና የሚያቀርቡት ሁሉ የረከሰ ነው።’ 15 “ ‘እንግዲህ ከዛሬ ጀምራችሁ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ከመነባበሩ በፊት የነበረውን ሁኔታ አስተውሉ። 16 አንድ ሰው ሃያ መስፈሪያ ወደሚሆን የእህል ክምር በመጣ ጊዜ ዐሥር ብቻ አገኘ፤ ዐምሳ ማድጋ የወይን ጠጅ ለመቅዳት ወደ መጭመቂያው በሄደ ጊዜ ሃያ ብቻ አገኘ። 17 የእጃችሁን ሥራ ሁሉ በዋግ፣ በአረማሞና በበረዶ መታሁት፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም’ ይላል እግዚአብሔር፤ 18 ‘ከዚህ ቀን ጀምሮ፣ ይኸውም ከዘጠነኛው ወር ሃያ አራተኛ ቀን ጀምሮ፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት እስከ ተጣለበት ቀን ድረስ ያለውን ዘመን አስተውሉ፤ ልብ ብላችሁም አስቡ፤ 19 በጐተራ የቀረ ዘር አሁንም ይገኛልን? የወይኑና የበለሱ ዛፍ፣ የሮማኑና የወይራው ዛፍ እስካሁን አላፈሩም። “ ‘ከዚህ ቀን ጀምሮ እባርካችኋለሁ።’ ” እግዚአብሔር ለዘሩባቤል የሰጠው ተስፋ 20 በወሩ ሃያ አራተኛ ቀን የእግዚአብሔር ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ ሐጌ መጣ፤ 21 “ለይሁዳ ገዥ ለዘሩባቤል ሰማያትንና ምድርን እንደማናውጥ ንገረው፤ 22 የመንግሥታትን ዙፋን እገለብጣለሁ፤ የባዕዳንን መንግሥታት ኀይል አጠፋለሁ፤ ሠረገሎችንና ሠረገለኞችን እገለብጣለሁ፤ ፈረሶችና ጋላቢዎቻቸውም በገዛ ወንድሞቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ። 23 “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዚያ ቀን ባሪያዬ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል ሆይ፤ እኔ እወስድሃለሁ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘እንደ ማተሚያ ቀለበቴ አደርግሃለሁ፤ እኔ መርጬሃለሁና’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.