ዘዳግም 7:25 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም የአማልክታቸውን ምስሎች በእሳት አቃጥል፤ በላያቸው የሚገኘውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ ለራስህ አታድርግ፤ አለዚያ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ስለ ሆነ ያሰናክልሃል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የተቀረጸውንም የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ በእነርሱ ላይ የተለበጠውን ብር ወይም ወርቅ አትመኝ፥ በጌታ አምላካችሁም ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትጠመድበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ጣዖቶቻቸውን በእሳት አቃጥል፤ በእነርሱ ላይ የተለበጠውን ብር ወይም ወርቅ የራስህ ንብረት አድርገህ ለመውሰድ ልብህ አይመኝ፤ ይህን ብታደርግ ወጥመድ ይሆንብሃል፤ እግዚአብሔርም አምልኮ ጣዖትን ስለሚጠላ ብርቱ ጥፋትን ያስከትልብሃል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ ከእነርሱም የተሠራባቸውን ብርንና ወርቅን፥ አትመኝ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትበድልበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የተቀረጸውንም የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ የተሠራባቸውን ብርና ወርቅ አትመኝ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትጠመድበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ። |
የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ወይም የርሱን ወንድ አገልጋይ ሆነ ሴት አገልጋይ፣ በሬውንም ሆነ አህያውን ወይም የርሱ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትመኝ።”
ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “ይህ ትክክል አይሆንም፤ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የምናቀርበው መሥዋዕት በግብጻውያን ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ ታዲያ በእነርሱ ዐይን አስጸያፊ የሆነውን መሥዋዕት ብናቀርብ አይወግሩንምን?
ከዚያም በብር የተለበጡትን ጣዖቶችህንና በወርቅ የተለበዱ ምስሎችህን ታዋርዳለህ፤ “ከዚህ ወግዱ!” ብለህም እንደ መርገም ጨርቅ ትጥላቸዋለህ።
ልብሱን ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራውን ወይም በእጅ የተጠለፈውን የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ወይም ደዌው ያለበትን ማንኛውንም ከቈዳ የተሠራ ዕቃ ያቃጥል፤ ደዌው ክፉ ነውና፤ ዕቃው ይቃጠል።
“ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤ የሰማይን ወፎች፣ የባሕርንም ዓሦች አጠፋለሁ፤ ለክፉዎችም እንቅፋት የሆኑትን ጣዖታት አጠፋለሁ።” “ማንኛውንም ሰው ከምድር ገጽ አስወግዳለሁ” ይላል እግዚአብሔር።
መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን በእሳት አቃጥሉ፤ የአማልክታቸውን ጣዖቶች ቈራርጣችሁ ጣሉ፤ ስማቸውንም ከእነዚያ ስፍራዎች ላይ አጥፉ።
በከተማዪቱ የተገኘውን የምርኮ ዕቃ ሁሉ በአደባባይዋ መካከል ላይ ሰብስበህ፣ ከተማዪቱን ከነምርኮዋ እንዳለ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገህ በሙሉ አቃጥል። ለዘላለም እንደ ፈረሰች ትቅር፤ ተመልሳም አትሠራ።
ለዝሙት ዐዳሪ ሴት ወይም ለወንደቃ የተከፈለውን ዋጋ ለማንኛውም ስእለት አድርገህ ለመስጠት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አታምጣ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ሁለቱንም ይጸየፋቸዋልና።
“የእጅ ጥበብ ባለሙያ የሠራውን፣ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ የሆነውን ምስል የሚቀርጽ ወይም ጣዖትን የሚያበጅ፣ በስውርም የሚያቆም ሰው የተረገመ ይሁን።” ሕዝቡም ሁሉ፣ “አሜን!” ይበል።
አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥህን ሕዝቦች ሁሉ ማጥፋት አለብህ፤ አትዘንላቸው፤ ወጥመድ ስለሚሆኑብህም አማልክታቸውን አታምልክ።
እንግዲህ በእነርሱ ላይ የምታደርጉት ይህ ነው፤ መሠዊያዎቻቸውን አፈራርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን ቍረጡ፤ ጣዖቶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ።
እስራኤላውያን ግን ዕርም የሆነውን ነገር ለራሳቸው በመውሰድ በደሉ፤ ይህም ከይሁዳ ነገድ የሆነው አካን የከርሚ ልጅ፣ የዘንበሪ ልጅ፣ የዛራ ልጅ ዕርም ከሆነው ነገር ስለ ወሰደ የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ልጆች ላይ ነደደ።
ከምርኮው ዕቃ መካከል ከሰናዖር የመጣ አንድ የሚያምር ካባ፣ ሁለት መቶ ሰቅል ብርና ክብደቱ ዐምሳ ሰቅል የሚሆን የወርቅ ቡችላ አይቼ ጐመጀሁ፤ ወሰድኋቸውም፤ ዕቃውም ብሩ ከታች ሆኖ፣ በድንኳኔ ውስጥ መሬት ተቀብሯል።”