ቈላስይስ 2:18 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ዐጕል ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ የሚወድድ ማንም ሰው እንዳያደናቅፋችሁ ተጠንቀቁ። እንደዚህ ያለ ሰው ስላየው ራእይ ከመጠን በላይ ራሱን እየካበ በሥጋዊ አእምሮው ከንቱ ሐሳብ ተሞልቶ ይታበያል፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ራስን ማዋረድና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባየውም ራእይ ላይ በጽኑ እየተመረኮዘ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በአጉል ትሕትናና መላእክትን በማምለክ የሚመካ ማንም ሰው ያለ ዋጋ እንዳያስቀራችሁ ተጠንቀቁ፤ እንዲህ ዐይነቱ ሰው ስለሚያየው ራእይ እየተመጻደቀ ከንቱና ሥጋዊ በሆነ አስተሳሰብ ይታበያል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በመታለልና ራስን ዝቅ በማድረግ ለመላእክት አምልኮ ትታዘዙ ዘንድ ወድዶ፥ በአላየውም በከንቱ የሥጋው ምክር እየተመካ የሚያሰንፋችሁ አይኑር። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ |
በእነርሱም ምትክ የምሽጎችን አምላክ ያከብራል፤ አባቶች የማያውቁትን አምላክ በወርቅ፣ በብር፣ በከበሩ ድንጋዮችና በውድ ስጦታዎች ያከብራል።
ይኸውም ፌጎር ላይ በተፈጸመው ድርጊትና በፌጎር ምክንያት በመጣው መቅሠፍት በተገደለችው በምድያማዊው አለቃ ልጅ፣ በእኅታቸው በከስቢ አታልለው የጠላትነት ሥራ ስለ ሠሩባችሁ ነው።”
እንደ እነዚህ ያሉት ሰዎች የሚያገለግሉት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ሆድ ነው። በለሰለሰ አንደበታቸውና በሽንገላ የዋሆችን ያታልላሉ።
አሁንም ሥጋውያን ናችሁ፤ በመካከላችሁ ቅናትና ክርክር አለ። ታዲያ፣ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? ተግባራችሁስ እንደ ማንኛውም ሰው ተግባር መሆኑ አይደለምን?
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ለእናንተ ጥቅም ብዬ በዚህ ጕዳይ እኔን ራሴንና አጵሎስን ምሳሌ አድርጌ አቅርቤላችኋለሁ፤ ይህንም ያደረግሁት፣ “ከተጻፈው አትለፍ” የሚለውን ከእኛ እንድትማሩ ነው። ስለዚህ አንዱን ሰው ከሌላው አብልጣችሁ አትመኩበት።
በሩጫ ውድድር የሚሮጡ ብዙዎች እንደ ሆኑ፣ ሽልማቱን የሚቀበለው ግን አንዱ ብቻ እንደ ሆነ አታውቁምን? ስለዚህ ሽልማቱን እንደሚቀበል ሰው ሩጡ።
ነገር ግን እባብ ሔዋንን በተንኰል እንዳሳታት ምናልባት የእናንተም ልቡና ተበላሽቶ ለክርስቶስ ካላችሁ ቅንነትና ንጽሕና እንዳትወሰዱ እሠጋለሁ።
ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜ፣ እኔ እንደምፈልገው ሆናችሁ ላላገኛችሁ እችላለሁ ወይም እናንተ እንደምትፈልጉኝ ሆኜ ላታገኙኝ ትችላላችሁ ብዬ እፈራለሁ፤ ምናልባትም በመካከላችሁ ጥል፣ ቅናት፣ ቍጣ፣ አድመኝነት፣ ስም ማጥፋት፣ ሐሜት፣ እብሪትና ሁከት ይኖራል ብዬ እሠጋለሁ።
እነዚህ ነገሮች በገዛ ራስ ላይ ከሚፈጥሩት የአምልኮ ስሜት፣ ከዐጕል ትሕትናና ሰውነትን ከመጨቈን አንጻር በርግጥ ጥበብ ያለባቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን የሥጋን ልቅነት ለመቈጣጠር አንዳች ፋይዳ የላቸውም።
በክርስቶስ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ወግና በዚህ ዓለም መሠረታዊ መንፈሳዊ ኀይሎች ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማግባቢያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ።
ዐይናቸው ቅንዝር የተሞላ በመሆኑ ኀጢአትን ከመሥራት አይቈጠቡም፤ ጽኑ ያልሆኑትን ነፍሳት ያስታሉ፤ ሥሥትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው!
ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከርሱ ጋራ ተጣሉ።
በመጀመሪያው አውሬ ስም ምልክቶችን እንዲያደርግ ሥልጣን ስለ ተሰጠው፣ በምድር የሚኖሩ ሰዎችን አሳተ፤ በሰይፍ ቈስሎ ለነበረው፣ ነገር ግን በሕይወት ለሚኖረው አውሬ ምስል እንዲያቆሙም አዘዛቸው።
እኔም ልሰግድለት በእግሩ ሥር ተደፋሁ፤ እርሱ ግን፣ “ተው! ይህን አታድርግ! እኔም ከአንተና የኢየሱስን ምስክር ከያዙት ወንድሞችህ ጋራ አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና” አለኝ።