1 ሳሙኤል 2:5 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ጠግበው የነበሩ ለእንጀራ ሲሉ ተገዙ፤ ተርበው የነበሩ ግን እንጀራ ጠገቡ፤ መካኒቱ ሰባት ልጆች ወልዳለች፤ ብዙ ወንዶች ልጆች ወልዳ የነበረችው ግን መከነች። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጠግበው የነበሩ አጥተው ለእንጀራ ተገዙ፤ ተርበው የነበሩ ግን ከራብ ዐርፈዋል። መካኒቱ ሰባት ወለደች፥ ብዙ የወለደችው ግን ብቻዋን ቀረች። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ጠግበው የነበሩ ተርበው ለምግብ ተገዝተዋል፤ ተርበው የነበሩ ግን ጠግበዋል፤ መኻኒቱ ሰባት ወለደች፤ የብዙዎች ልጆች እናት የነበረችው ብቻዋን ቀረች። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እንጀራ ጠግበው የነበሩ ተራቡ፤ ተርበውም የነበሩ ጠገቡ፤ መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው መውለድ አልቻለችም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ጠግበው የነበሩ እንጀራ አጡ፥ ተርበው የነበሩ ከራብ ዐርፈዋል፥ መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው ደክማለች። |
“አንቺ መካን፣ አንቺ ልጅ ወልደሽ የማታውቂ፣ ዘምሪ፤ እልል በዪ፤ በደስታ ጩኺ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፣ ባል ካላት ሴት ይልቅ፣ የፈቷ ልጆች ይበዛሉና” ይላል እግዚአብሔር።
የሰባቶቹ እናት ትዝለፈለፋለች፤ ትንፋሿም ይጠፋል፤ ገና ቀን ሳለ ፀሓይዋ ትጠልቃለች፤ እርሷም ታፍራለች፤ ትዋረዳለችም፤ የተረፉትንም በጠላቶቻቸው ፊት፣ ለሰይፍ እዳርጋቸዋለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር።
“አብርሃም ግን እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፤ አንተ በምድራዊ ሕይወትህ ዘመን መልካም ነገሮችን እንደ ተቀበልህ፣ አልዓዛርም ደግሞ ክፉ ነገሮችን እንደ ተቀበለ አስታውስ፤ አሁን ግን እርሱ እዚህ ሲጽናና፣ አንተ በሥቃይ ላይ ትገኛለህ።
እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ “አንቺ የማትወልጅ መካን ሆይ፤ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፣ በእልልታ ጩኺ፤ ባል ካላት ይልቅ፣ የብቸኛዪቱ ልጆች በዝተዋልና።”
ስለዚህ ሐና ፀነሰች፤ የእርግዝናዋ ወራት በተፈጸመ ጊዜም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም፤ “ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ” ስትል ሳሙኤል አለችው።