1 ሳሙኤል 15:9 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም ነገር ግን ሳኦልና ሰራዊቱ አጋግን፣ ምርጥ ምርጡን በግና የቀንድ ከብት፣ የሰባውን ጥጃና ጠቦት፣ መልካም የሆነውን ሁሉ ሳይገድሉ ተውት። እነዚህን ፈጽመው ለማጥፋት ፈቃደኞች አልነበሩም፤ ነገር ግን የተናቀውንና የማይጠቅመውን ሁሉ አጠፉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ነገር ግን ሳኦልና ሠራዊቱ አጋግን፥ ምርጥ ምርጡን በግና የቀንድ ከብት፥ የሰባውን ጥጃና ጠቦት፥ መልካም የሆነውን ሁሉ ሳይገድሉ ተውት። እነዚህን ፈጽመው ለማጥፋት ፈቃደኞች አልነበሩም፤ ነገር ግን የተናቀውንና የማይጠቅመውን ሁሉ አጠፉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ነገር ግን ሳኦልና ሠራዊቱ የአጋግን ሕይወት አተረፉ፤ እንዲሁም ምርጥ ምርጥ የሆኑትን በጎችና የቀንድ ከብቶች፥ የሰቡ ሰንጋዎችንና ጠቦቶችን ከዚህም ጋር መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ አላጠፉም፤ እነርሱም ያጠፉት የማይረባውንና የማይጠቅመውን ነገር ብቻ ነበር። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ነገር ግን ሳኦልና ሕዝቡ ሁሉ አጋግን፥ ከከብቱና ከበጉ መንጋ መልካም መልካሙን፥ እህሉንም፥ ወይኑንም፥ መልካም የሆነውን ሁሉ አዳኑ። ፈጽመው ሊያጠፉአቸውም አልወደዱም፤ ነገር ግን የተናቀውን ሁሉ ፈጽመው አጠፉት። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ነገር ግን ሳኦልና ሕዝቡ ለአጋግ፥ ለተመረጡትም በጎችና በሬዎች ለሰቡትም ጥጆችና ጠቦቶች፥ ለመልካሞቹም ሁሉ ራሩላቸው፥ ፈጽሞ ሊያጠፉአቸውም አልወደዱም፥ ነገር ግን ምናምንቴንና የተናቀውን ሁሉ ፈጽመው አጠፉት። |
ቤን ሃዳድም፣ “አባቴ ከአባትህ የወሰዳቸውን ከተሞች እመልሳለሁ፤ አባቴ በሰማርያ እንዳደረገው ሁሉ፣ አንተም በደማስቆ የራስህን ገበያ ማቋቋም ትችላለህ” አለው። አክዓብም፣ “እንግዲያውስ ስምምነት አድርገን በነጻ እለቅቅሃለሁ” አለው፤ ስለዚህም ከርሱ ጋራ የውል ስምምነት አድርጎ ለቀቀው።
እናንተ ግን ዕርም ከሆኑት ነገሮች አንዳች በመውሰድ በራሳችሁ ላይ ጥፋት እንዳታመጡ እጃችሁን ሰብስቡ፤ አለዚያ የእስራኤልን ሰፈር ለጥፋት ትዳርጋላችሁ፤ ክፉ ነገር እንዲደርስበትም ታደርጋላችሁ፤
ከምርኮው ዕቃ መካከል ከሰናዖር የመጣ አንድ የሚያምር ካባ፣ ሁለት መቶ ሰቅል ብርና ክብደቱ ዐምሳ ሰቅል የሚሆን የወርቅ ቡችላ አይቼ ጐመጀሁ፤ ወሰድኋቸውም፤ ዕቃውም ብሩ ከታች ሆኖ፣ በድንኳኔ ውስጥ መሬት ተቀብሯል።”
ሳኦልም፣ “ሰራዊቱ ከአማሌቃውያን ማርከው ያመጧቸው ናቸው፤ ምርጥ ምርጦቹ በጎችና በሬዎች ለእግዚአብሔር ለአምላክህ መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳይገድሉ የተዉአቸው ናቸው፤ የቀሩትን ግን በሙሉ አጥፍተናል” ብሎ መለሰ።
አሁንም ሂድ፤ አማሌቃውያንን ውጋ፤ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፤ አንዱንም አታስቀር፤ ወንዱንና ሴቱን፣ ልጁንና ሕፃኑን፣ የቀንድ ከብቱንና በጉን፣ ግመሉንና አህያውን ግደል።’ ”