ዘዳግም 9:18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚህም በኋላ እንደገና አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ምንም ነገር ሳልበላና ሳልጠጣ በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፍቼ ቈየሁ። ይህንንም ያደረግኹት እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ኃጢአት ሠርታችሁ እርሱን በማስቈጣታችሁ ምክንያት ነበር። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን በመፈጸም ለቍጣ እንዲነሣሣ የሚያደርገውን ኀጢአት ሁሉ ስለ ሠራችሁ፣ እህል ውሃ ሳልቀምስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት እንደ ገና በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፋሁ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከዚህም በኋላ እንደገና አርባ ቀንና አርባ ሌሊት እህል ሳልቀምስና ውኃ ሳልጠጣ በጌታ ፊት በግንባሬ ተደፍቼ ቆየሁ። ይህንንም ያደረግኹት ስለ ሠራችሁት ኃጢአት ሁሉ፥ እርሱንም ለማስቆጣት በጌታ ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ስላደረጋችሁ ነበር። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ስለ ሠራችሁት ኀጢአት ሁሉ፥ እርሱንም ለማስቈጣት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ስላደረጋችሁ፥ እንደ ፊተኛው በእግዚአብሔር ፊት አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ዳግመኛ ለመንሁ፤ እንጀራ አልበላሁም፥ ውኃም አልጠጣሁም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ስለ ሠራችሁት ኃጢአት ሁሉ፥ እርሱንም ለማስቆጣት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ስላደረጋችሁ፥ እግዚአብሔር ሊያጠፋችሁ ከተቈጣባችሁ ከቍጣውና ከመዓቱ የተነሣ ስለ ፈራሁ፥ እንደ ፊተኛው በእግዚአብሔር ፊት አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ወደቅሁ፤ እንጀራ አልበላሁም፥ ውኃም አልጠጣሁም። እግዚአብሔርም በዚያን ጊዜ ደግሞ ሰማኝ። |
ኤልያስም ተነሥቶ ምግቡን በላ፥ ውሃውንም ጠጣ፤ ከዚያም ምግብ ባገኘው ኀይል እስከ ተቀደሰው የሲና ተራራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሙሉ ተጓዘ፤
ቀጥሎም ዕዝራ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ከነበረው ስፍራ በመነሣት የኤልያሺብ ልጅ ዮሐናን ወደሚኖርባቸው ክፍሎች ገባ፤ ምርኮኞቹ እምነት በማጓደል ስለ ፈጸሙትም በደል ሁሉ እያዘነ ሌሊቱን በዚያው አነጋ፤ እህልም ሆነ ውሃ አልቀመሰም።
ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሕዝቦቹን ለማጥፋት ዐቅዶ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የመረጠው ሙሴ በመካከል በመቆም፥ እንዳያጠፋቸውና ቊጣውንም እንዲመልስ እግዚአብሔርን ለመነ።
ሙሴም ምንም ሳይበላና ሳይጠጣ ከእግዚአብሔር ጋር አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየ፤ ጌታም በጽላቶቹ ላይ የቃል ኪዳን ቃላት የሆኑትን ዐሥሩን ትእዛዞች ጻፈ።
እንዲህም አለ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝቼ ከሆነ ከእኛ ጋር አብረህ እንድትወጣ እለምንሃለሁ፤ ይህ ሕዝብ እልኸኛ ነው፤ ነገር ግን ኃጢአታችንንና ክፉ ሥራችንን ሁሉ ይቅር በል፤ የራስህ ሕዝብ አድርገህ ተቀበለን።”
“እኔም ከዚህ በፊት ባደረግሁት ዐይነት እንደገና በተራራው ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በመጸለይ ቈየሁ፤ እግዚአብሔርም እንደገና ልመናዬን ሰምቶ አንተን ላለማጥፋት ፈቀደ።
“ከዚያም ሁሉ የተነሣ በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፍቼ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ፤ ይህንንም ያደረግኹት እርሱ ‘እደመስሳችኋለሁ’ ብሎ ስለ ነበር ነው፤
እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የገባው ቃል ኪዳን የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላቶች ለመቀበል እኔ ወደ ተራራው ወጥቼ ነበር፤ በዚያም ምንም ነገር ሳልበላና ሳልጠጣ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ።