ኢያሱ 11:3 - መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በምሥራቅና በምዕራብም ወዳለው ወደ ከነዓናዊው፥ ወደ አሞራዊውም፥ ወደ ኬጢያዊውም፥ ወደ ፌርዛዊውም፥ በተራራማውም አገር ወዳለው ወደ ኢያቡሳዊው፥ ከአርሞንዔምም በታች በምጽጳ ወዳለው ወደ ኤዊያዊው ላከ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ደግሞም በምሥራቅና በምዕራብ ወደሚገኙት ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ ፌርዛውያንና በኰረብታማው አገር ወደሚኖሩት ወደ ኢያቡሳውያን፣ እንዲሁም ደግሞ በምጽጳ ምድር በአርሞንዔም ተራራ ግርጌ ወዳሉት ወደ ኤዊያውያን ነገሥታት መልእክት ላከ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በምሥራቅና በምዕራብም ወዳለው ወደ ከነዓናዊው፥ ወደ አሞራዊውም፥ ወደ ኬጢያዊውም፥ ወደ ፌርዛዊውም፥ በተራራማውም አገር ወዳለው ወደ ኢያቡሳዊው፥ ከአርሞንዔምም በታች በምጽጳ ወዳለው ወደ ኤዊያዊው ላከ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እንዲሁም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ ወደሚገኙት ወደ ከነዓናውያን፥ ወደ አሞራውያን፥ ወደ ሒታውያን፥ ወደ ፈሪዛውያንና፥ በኮረብታማው አገር ወደሚገኙት ወደ ኢያቡሳውያን፥ እንዲሁም በምጽጳ ምድር በሔርሞን ተራራ ግርጌ ወደሚገኙት ወደ ሒዋውያን ሁሉ መልእክት ላከ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በምሥራቃዊ ባሕር ዳርቻ ወዳለው ወደ ከነዓናዊው፥ ወደ አሞሬዎናዊውም፥ ወደ ኬጤዎናዊውም፥ ወደ ፌርዜዎናዊውም፥ በተራራማውም ሀገር ወዳለው ወደ ኢያቡሴዎናዊው፥ በቆላማውና በመሴፋ ወዳለው ወደ ኤዌዎናዊዉም ላከ። |
የእግዚአብሔርም መልአክ ኢየሩሳሌምን ያጠፋት ዘንድ እጁን በዘረጋ ጊዜ እግዚአብሔር ስለ ክፉው ነገር አዘነ፥ ሕዝቡንም የሚያጠፋውን መልአክ፦ እንግዲህ በቃህ፥ እጅህን መልስ አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ነበረ።
ንጉሡም አሳ በይሁዳ ሁሉ ላይ አዋጅ ነገረ፤ ማንም ነጻ አልነበረም፤ ባኦስም የሠራበትን የራማን ድንጋይና እንጨት ወሰዱ፤ ንጉሡም አሳ የብንያምን ጌባንና ምጽጳን ሠራበት።
ሙሽራዬ ሆይ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፥ ከአማና ራስ ከሳኔርና ከኤርሞን ራስ፥ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች።
እኔም፥ እነሆ፥ ወደ እኛ በሚመጡት ከለዳውያን ፊት እቆም ዘንድ በምጽጳ እኖራለሁ፥ እናንተ ግን ወይንንና የበጋ ፍሬ ዘይትንም አከማቹ፥ በየዕቃችሁም ውስጥ ክተቱ፥ በያዛችኋቸውም ከተሞቻችሁ ተቀመጡ።
በደቡብም ምድር አማሌቅ ተቀምጦአል፤ በተራሮቹም ኬጢያዊና ኢያቡሳዊ አሞራዊም ተቀምጠዋል፤ ከነዓናዊም በባሕር ዳርና በዮርዳኖስ አጠገብ ተቀምጦአል።
አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር ባመጣህ ጊዜ፥ ከፊትህም ብዙ አሕዛብን፥ ከአንተ የበለጡትን የበረቱትንም ሰባቱን አሕዛብ፥ ኬጢያዊውን ጌርጌሳዊውንም አሞራዊውንም ከነዓናዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም ባወጣ ጊዜ፥
እስከ ሴይርም ከሚያወጣው ወና ከሆነው ተራራ ጀምሮ ከአርሞንዔም ተራራ በታች በሊባኖስም ሸለቆ ውስጥ እስካለው እስከ በአልጋድ ድረስ፥ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ይዞ መታቸው፥ ገደላቸውም።
እግዚአብሔርም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ መቱአቸውም፥ ወደ ታላቂቱም ሲዶና፥ ወደ ማሴሮንም፥ በምሥራቅም በኩል ወዳለው ወደ ምጽጳ ሸለቆ አሳደዱአቸው፥ ማንንም ሳያስቀሩ መቱአቸው።
በኢየሩሳሌም የተቀመጡትን ኢያቡሳውያንን ግን የይሁዳ ልጆች ሊያሳድዱአቸው አልተቻላቸውም፥ ኢያቡሳውያንም እስከ ዛሬ በይሁዳ ልጆች መካከል በኢየሩሳሌም ውስጥ ተቀምጠዋል።
ኢያሱም አለ፦ ሕያው አምላክ በመካከላችሁ እንደ ሆነ፥ እርሱም ከፊታችሁ ከነዓናዊውን ኬጢያዊውንም ኤዊያዊውንም ፌርዛዊውንም ጌርጌሳዊውንም አሞራዊውንም ኢያቡሳዊውንም ፈፅሞ እንዲያወጣ በዚህ ታውቃላችሁ።
የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወጡ፥ ማኅበሩም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ፥ ከገለዓድም አገር ሰዎች ጋር፥ ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ እንደ አንድ ሰው ሆነው ተሰበሰቡ።
የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ስላልወጣ ሰው፦ እርሱ ፈጽሞ ይገደል ብለው ታላቅ መሐላ ምለው ነበርና፦ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ወደ ጉባኤ ወደ እግዚአብሔር ያልወጣ ማን ነው? አሉ።
እነርሱም፦ ከእስራኤል ነገድ ወደ እግዚአብሔር ወደ ምጽጳ ያልወጣ ማን ነው? አሉ። እነሆም፥ ከኢያቢስ ገለዓድ ወደ ሰፈሩ ወደ ጉባኤ ማንም አልወጣም ነበር።
አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥ ከነዓናውያንም ሁሉ፥ ሲዶናውያንም፥ ከበኣልአርሞንዔም ተራራ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ በሊባኖስ ተራራ የሚኖሩትም ኤዊያውያን።