ኢያሱ 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኢያሱ ያቢንንና የጦር ተባባሪዎቹን ድል ማድረጉ 1 የሐጾር ንጉሥ ያቢን የእስራኤልን ድል አድራጊነት በሰማ ጊዜ፥ ወደ ማዶን ንጉሥ ዮባብ፥ ወደ ሺምሮንና ወደ አክሻፍ ነገሥታት፥ 2 በሰሜን በኩል በኮረብታማው አገር፥ ከገሊላ ባሕር በስተ ደቡብ ወደ ነበሩበት ነገሥታት፥ በዮርዳኖስ ሸለቆ፥ በኮረብታዎቹ ግርጌ በስተምዕራብም በፎት ዳር ወደ ነበሩት ነገሥታት ላከ። 3 እንዲሁም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ ወደሚገኙት ወደ ከነዓናውያን፥ ወደ አሞራውያን፥ ወደ ሒታውያን፥ ወደ ፈሪዛውያንና፥ በኮረብታማው አገር ወደሚገኙት ወደ ኢያቡሳውያን፥ እንዲሁም በምጽጳ ምድር በሔርሞን ተራራ ግርጌ ወደሚገኙት ወደ ሒዋውያን ሁሉ መልእክት ላከ። 4 እነርሱም ከነወታደሮቻቸው ስለ መጡ፥ የሠራዊቱ ብዛት እንደ ባሕር አሸዋ ሆነ፤ ከዚህም ሁሉ ጋር ብዙ ፈረሶችና ሠረገሎች ነበራቸው። 5 እነዚህም ሁሉ ነገሥታት ኀይላቸውን አስተባብረው እስራኤላውያንን ለመውጋት በሜሮም ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ። 6 እግዚአብሔርም ኢያሱን “እነርሱን አትፍራ፤ ስለ እስራኤል በመዋጋት ነገ ይህን ጊዜ ሁሉንም እንደ ሞቱ አድርጌ በእስራኤል እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ አንተም የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ትቈርጣለህ፤ ሠረገሎቻቸውንም በእሳት ታቃጥላለህ” አለው። 7 ስለዚህም ኢያሱና መላ ሠራዊቱ ዘምተው በሜሮም ድንገተኛ አደጋ ጣሉባቸው። 8 እግዚአብሔርም እስራኤላውያን በእነርሱ ላይ ድልን እንዲቀዳጁ አደረጋቸው፤ እስራኤላውያንም መተው በሰሜን እስከ ሚስረፎትማይምና እስከ ታላቂቱ ሲዶና፥ በምሥራቅም እስከ ምጽጳ ሸለቆ ድረስ አሳደዱአቸው፤ ከእነርሱም አንድ ሰው እንኳ ሳይተርፍ ሁሉንም ፈጁአቸው። 9 ኢያሱም በእነርሱ ላይ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። ይኸውም የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ቈረጠ፤ ሠረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጠለ። 10 ኢያሱም ወደ ኋላ ተመልሶ ሐጾርን ድል ነሥቶ ያዘ፤ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለ፤ ሐጾር በዚያን ዘመን ከነበሩት የዘውድ መንግሥታት ሁሉ የሚበልጥ ኀይል ያላት ነበረች። 11 እስራኤላውያን በሐጾር የተገኘውን ሰው ሁሉ ስለ ገደሉ በሕይወት የተረፈ አልነበረም፤ ከተማይቱም በእሳት ተቃጠለች። 12 የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ባዘዘው መሠረት ኢያሱ እነዚህን ከተሞችና ንጉሦቻቸውን ሁሉ ማረከ፤ በሰይፍም መታቸው፤ ፈጽሞም አጠፋቸው። 13 ይሁን እንጂ ኢያሱ ካቃጠላት ከሐጾር በቀር እስራኤላውያን በኮረብታ ላይ የተሠሩ ከተሞችን አላቃጠሉም። 14 የእስራኤል ሕዝብ ዋጋ ያለውን ንብረትና ከብቱን ሁሉ ከእነዚህ ከተሞች ወስደው የራሳቸው ንብረት አደረጉት፤ ሰዎቹን ሁሉ ግን በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ፤ አንድ ሰው እንኳ ሳይቀር ሁሉንም ገደሉ። 15 እግዚአብሔር ትእዛዙን ለአገልጋዩ ለሙሴ ሰጠ፤ ሙሴም ለኢያሱ ሰጠ፤ ኢያሱም ትእዛዞችን ፈጸመ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ኢያሱ ሁሉን ነገር አደረገ፤ አንዳችም አላስቀረም። ኢያሱ የያዛቸው አገሮች ዝርዝር 16 ኢያሱ እነዚያን አገሮች፦ ተራራማውን፥ ኔጌብን፥ የጎሼንን ምድር፥ ቈላማውን፥ የዮርዳኖስን ሸለቆ፥ ቈላማውንና ደጋማውን የእስራኤልን ምድር ሁሉ ያዘ። 17 እርሱም ወደ ኤዶም ከሚያወጣው ከሐላቅ ተራራ ጀምሮ ከሔርሞን ተራራ በታች እስከ ሊባኖስ ሸለቆ እስከ ባዓልጋድ ድረስ ያሉትን ነገሥታት ሁሉ ማርኮ መታቸው፤ ገደላቸውም፤ 18 ኢያሱም ከእነዚህ ነገሥታት ሁሉ ጋር ይዋጋ ነበር። 19 ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ስምምነት አድርጋ በሰላም የኖረች አገር ከሒዋውያን ወገን የገባዖን ኑዋሪዎች በቀር ሌላ አልነበረም፤ ሌሎቹ በሙሉ በጦርነት ድል ሆነው የተያዙ ናቸው። 20 እነዚህም ሁሉ ከእስራኤላውያን ጋር ጦርነት እንዲገጥሙ እግዚአብሔር ልባቸውን እልኸኛ አድርጎ አነሣሣቸው። ስለዚህም በአጠቃላይ እንዲደመሰሱ ተፈርዶባቸው ያለ ምሕረት ተገደሉ፤ እግዚአብሔርም አስቀድሞ ለሙሴ የሰጠው ትእዛዝ ይኸው ነበር። 21 በዚህን ጊዜ ዘምቶ ረጃጅሞች የሆኑትን የዐናቅን ዘሮች ደመሰሰ፤ እነርሱም በኮረብታማው አገር በኬብሮን፥ በደቢር፥ በዐናብ፥ በይሁዳና በእስራኤል ኮረብታማ አገሮች የሚኖሩ ነበሩ። ኢያሱ እነዚህን ሕዝቦችና ከተሞቻቸውን ሁሉ ደመሰሰ። 22 ከዐናቅ ዘሮች በእስራኤል ምድር የተረፈ አልነበረም፤ ነገር ግን ጥቂቶች ብቻ በጋዛ፥ በጋትና በአሽዶድ ይኖሩ ነበር። 23 እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ኢያሱ ምድሩን ሁሉ በእጁ አደረገ፤ ለእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ድርሻ ርስት አድርጎ በመስጠት ለእስራኤላውያን በሙሉ አከፋፈለ። ስለዚህም ምድሪቱ ከጦርነት ዐረፈች። |