ዘሌዋውያን 1:2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር መባ በሚያቀርቡበት ጊዜ ሊጠብቁት የሚገባ ሥርዓት ይህ ነው፦ እያንዳንዱ ሰው ከቀንድ ከብትም ሆነ፥ ከበግ ወይም ከፍየል ወገን ማንኛውንም ዐይነት መባ በሚያቀርብበት ጊዜ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ከእናንተ ማንም ሰው ለእግዚአብሔር ከእንስሳ ወገን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ከላሙ፣ ከበጉ ወይም ከፍየሉ መንጋ መካከል ያቅርብ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ትነግራቸዋለህ፦ ከእናንተ ማናቸውም ሰው ለጌታ መባ ሲያቀርብ፥ መባችሁን ከእንስሳ ወገን ከሆኑ ከበሬ ወይም ከበግ መንጋ ታቀርባላችሁ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ከእናንተ ለእግዚአብሔር መባ የሚያቀርብ ሰው ቢኖር መባችሁን ከእንስሳ ወገን ከላሞች ወይም ከበጎች ታቀርባላችሁ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራችው፦ ከእናንተ ማናቸውም ሰው ለእግዚአብሔር መባ ሲያቀርብ መባችሁን ከእንስሳ ወገን ከላሞች ወይም ከበጎች ታቀርባላችሁ። |
በተጨማሪም ዘወትር በሙሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ በወር መባቻ በዓልና በሌሎችም የተቀደሱ የእግዚአብሔር በዓላት የሚቀርብ መሥዋዕትን በበጎ ፈቃድ ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ ጋር አቀረቡ።
ለእኔ ከጭቃ የተሠራ መሠዊያ አብጁልኝ፤ በእርሱም ላይ ከበጎቻችሁ፥ ከፍየሎቻችሁና ከከብቶቻችሁ መርጣችሁ የሚቃጠልና የአንድነት መሥዋዕት አድርጋችሁ ሠዉበት፤ ስሜ እንዲታሰብበት በወሰንኩት ስፍራ ሁሉ ወደ እናንተ መጥቼ እባርካችኋለሁ፤
ለሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ስለ ስእለት መፈጸም ለሚቀርብ መሥዋዕት ወይም በበጎ ፈቃድ ለሚቀርብ መሥዋዕት ወይም በተለመዱት የሃይማኖት በዓላት ላይ ለሚቀርብ መሥዋዕት፥ ከከብት ወይም ከበግ መንጋዎች ለእግዚአብሔር ታቀርባላችሁ፤ እንደዚህ ያለውም የምግብ ቊርባን መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል፤
ያ ሰው ሚስቱን ወደ ካህኑ ያምጣት፥ ስለ እርስዋ የሚፈልገውንም አንድ ኪሎ የገብስ ዱቄት ቊርባን ያምጣ፤ የቅናት ቊርባን ማለት በደልን የሚገልጥ የእህል ቊርባን ስለ ሆነ ዘይት አያፍስስበት፤ ዕጣንም አያድርግበት።
እናንተ ግን እንዲህ ትላላችሁ፤ ‘አንድ ሰው ለአባቱ ወይም ለእናቱ በመርዳት ፈንታ ለአባቱና ለእናቱ ማድረግ የሚገባውን ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ያቀረብኩት መባ ነው፤’ ቢላችሁ፥
እንግዲህ ወንድሞቼ ሆይ! እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ፥ ሕያውና የተቀደሰ መሥዋዕት አድርጋችሁ ሁለንተናችሁን እንድታቀርቡ በመሐሪው በእግዚአብሔር ስም እለምናችኋለሁ፤ ይህም ማቅረብ የሚገባችሁ ቅንነት ያለው እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልግሎት ነው።
ስለዚህ እግዚአብሔር በጸጋው የሰጠንን ልዩ ልዩ ስጦታ በሥራ ላይ እናውል፤ ስጦታችን የእግዚአብሔርን ቃል ማወጅ ከሆነ በእምነታችን መጠን የእግዚአብሔርን ቃል እናውጅ።
ክርስቶስ እንደ ወደደንና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መልካም መዓዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ኑሩ።