ኢሳይያስ 51:11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ስለዚህ አንተ እግዚአብሔር የተቤዠኻቸው እየዘመሩ ወደ ኢየሩሳሌም ይመለሳሉ፤ ዘላቂ ደስታንም እንደ ዘውድ ይቀዳጃሉ፤ ሐሴትና ደስታንም ያገኛሉ፤ ማዘንና መቃተት ግን ከእነርሱ ይወገዳል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔር የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤ በዝማሬ ወደ ጽዮን ይገባሉ፤ ዘላለማዊ ደስታን ይጐናጸፋሉ፤ ደስታና ሐሤት ይቀድማሉ፤ ሐዘንና ትካዜም ይሸሻሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ የተቤዣቸው ይመለሳሉ ወደ ጽዮንም ይመጣሉ፤ የዘለዓለምም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ልቅሶም ይሸሻል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤ ወደ ጽዮንም በደስታና በሐሤት ይመጣሉ፤ የዘለዓለምም ክብር በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፤ ኀዘንና ልቅሶም ይወገዳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ ወደ ጽዮንም ይመጣሉ፥ የዘላለምም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፥ ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ልቅሶም ይሸሻል። |
እግዚአብሔር የግብጽን ባሕረ ልሳን ያደርቃል፤ ማንም ሰው በእግሩ መሻገር እንዲችል የኤፍራጥስን ወንዝ በኀይለኛ ነፋስ መትቶ ወደ ትናንሽ ሰባት ጅረቶች ይከፋፍለዋል።
ልዑል እግዚአብሔር የሞትን ኀይል ለዘለዓለም ያጠፋል! ከሰዎችም ሁሉ ዐይን እንባን ያብሳል፤ ወገኖቹ በዓለም ሁሉ ላይ የተቀበሉትን ኀፍረት ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ራሱ ይህን ተናግሮአል።
እግዚአብሔር የታደጋቸው ሰዎች ተመልሰው ይመጣሉ፤ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይገባሉ፤ ዘወትር የደስታን ዘውድ ይቀዳጃሉ፤ ተድላና ደስታንም ያገኛሉ፤ ማዘንና መቃተት ከእነርሱ ይርቃል።
ሰማያት ሆይ! እግዚአብሔር ሕዝቡን እስራኤልን በማዳን ክብሩን ገልጦአልና በደስታ ዘምሩ፤ ምድርም ከታች እልል በዪ፤ ተራራዎች፥ ጫካዎችና በውስጣቸው የምትገኙ ዛፎች ሁሉ የደስታ ድምፅ እያሰማችሁ ፈንድቁ።
እንግዲህ ከባቢሎን ወጥታችሁ ሽሹ፤ “እግዚአብሔር አገልጋዩን እስራኤልን አድኖአል” የሚለውን የምሥራች ቃል በደስታ አብሥሩ፤ በየስፍራውም እንዲታወቅ አድርጉ።
“እናንተም ከባቢሎን በደስታ ወጥታችሁ፥ በሰላም ወደ ሀገራችሁ እንድትመለሱ ትደረጋላችሁ፤ ተራራዎችና ኰረብቶች በፊታችሁ በመዘመር ይፈነድቃሉ፤ የሜዳ ዛፎችም በእጆቻቸው ያጨበጭባሉ።
ኀፍረታቸው እጥፍ ስለ ነበረ፤ ውርደትም የእነርሱ ዕድል ፈንታ መሆኑ ስለ ታወጀ ስለዚህ ድርሻቸው እጥፍ ይሆናል፤ ዘለዓለማዊ ደስታም ያገኛሉ።
አገልጋዮቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ፤ እናንተ ግን ከልብ ሐዘን የተነሣ ታላቅሳላችሁ፤ ከመንፈስም ጭንቀት የተነሣ ዋይ፥ ዋይ ትላላችሁ።
ልጃገረዶቻቸውም በደስታ ይጨፍራሉ፤ ወንዶች ወጣቶችና ሽማግሌዎችም ደስ ይላቸዋል፤ አጽናናቸዋለሁ፤ ለቅሶአቸውን ወደ ደስታ፥ ሐዘናቸውንም ወደ ሐሴት እለውጣለሁ፤
በዚህ ቦታ የተድላና የደስታ፥ የሠርግ ዘፈን ድምፅ እንደገና ይሰማል፤ ከምርኮ ለተመለሱትም ቀድሞ የነበራቸውን ንብረታቸውን ስለምመልስላቸው የምስጋና መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደሴ በሚመጡበት ጊዜ፥ ‘የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ እርሱ ቸር ነውና፥ ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ነውና’ እያሉ በከፍተኛ ድምፅ ይዘምራሉ። ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
ከዚህ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የመጀመሪያው ሰማይና የመጀመሪያይቱ ምድር አልፈው ነበር፤ ባሕርም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።