ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ተግሣጽ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ነገ የሚያመጣውን ምን እንደሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ። 2 ሌላ ያመስግንህ እንጂ አፍህ አይደለም፥ ባዕድ ሰው እንጂ ከንፈርህ አይደለም። 3 ድንጋይ ከባድ ነው፥ አሸዋም ሸክሙ ጽኑ ነው፤ ከሁለቱ ግን ያላዋቂ ቍጣ ይከብዳል። 4 ለቍጡና ቍጣን ለሚያፋጥን ምሕረት የለውም፥ ቀናተኛን ግን የሚተካከለው የለም። 5 የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል። 6 ከጠላት መልካም አሳሳም የወዳጅ ንክሻ ይሻላል። 7 የጠገበች ሰውነት የማር ወለላን ትንቃለች፤ ለተራበች ሰውነት ግን የመረረ ነገር ሁሉ ጣፋጭ ሆኖ ይታያታል። 8 ከጎጆዋ ወጥታ እንደምትበርር ወፍ እንደዚሁ ከሀገር ወጥቶ እንግዳ የሚሆን ተገዥ ይሆናል። 9 በሽቱና በዕጣን፥ በወይንም ልብ ደስ ይሰኛል፥ እንዲሁ ነፍስ በወዳጅ ምክር ደስ ይላታል። 10 ወዳጅህንና የአባትህን ወዳጅ አትተው፥ አስቀድመህም ሳትነግረው በመከራህ ቀን ወደ ወንድምህ ቤት አትግባ። የቀረበ ወዳጅ ከራቀ ወንድም ይሻላል። 11 ልጄ ሆይ፥ ልቤ ደስ ይለው ዘንድ ጠቢብ ሁን፥ የሽሙጥንም ቃል ከአንተ አርቅ። 12 ዐዋቂ ሰው ክፋቶች በመጡበት ጊዜ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን ተከራክረው ጥፋትን ያመጣሉ። 13 የሌላውን የሚያጠፋ ጠላት መጥትዋልና ልብስህን አርቅ። 14 ባልንጀራውን በታላቅ ቃል ማለዳ የሚመርቅ ሰው፥ ከሚራገመው የሚተወው የለም። 15 ፍሳሽ በክረምት ወራት ሰውን ከቤቱ ያወጣዋል፥ እንደዚሁም ነዝናዛ ሴት ባልዋን ከመልካም ቤቱ ታስወጣለች። 16 የደቡብ ነፋስ ጽኑ ነው፥ በስሙ ግን ቀኝ ይባላል። 17 ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል። 18 በለስን የተከለ ፍሬዋን ይበላል፥ ጌታውንም የሚጠብቅ ይከብራል። 19 ፊት ከፊት ጋር እንደማይመሳሰል፥ እንዲሁም የሰው ልብ አይመሳሰልም። 20 ሲኦልና ሞት እንደማይጠግቡ፥ እንዲሁ የሰው ዐይኖች አይጠግቡም። በዐይኑ የሚገላምጥ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነው፤ ትምህርት የሌላቸውም አንደበታቸውን አይገቱም። 21 ወርቅና ብር በእሳት ግለት ይፈተናሉ፥ ሰውም በሚያመሰግኑት ሰዎች አፍ ይፈተናል። የኃጥእ ልቡ ክፋትን ትፈልጋለች፥ ቀና ልቡና ግን ዕውቀትን ትሻለች። 22 አላዋቂን በማዋረድ በጉባኤ መካከል ብትገርፈው፥ አላዋቂነቱን አታስወግድለትም። 23 የበጎችህን መንፈስ አስተውለህ ዕወቅ፥ በከብቶችህም ላይ ልብህን አኑር። 24 ግዛትም፥ ኀይልም ለዘለዓለም ለሰው አይደለም፥ ከትውልድ ወደ ትውልድ አይተላለፍምና። 25 የምድረ በዳ ልምላሜን ጠብቅ፥ ደረቅ ሣርንም እጨድ፥ የተራራውንም ሣር ሰብስብ። 26 በጎችን ለልብስ ገንዘብ ታደርግ ዘንድ፥ መንጋዎችህም ይበዙ ዘንድ መስኩን ጠብቅ። 27 ልጄ ሆይ፥ ከእኔ ዘንድ የጸናች ቃል አለችህ፥ ለሕይወትህና ለቤተ ሰቦችህም ሕይወት የፍየል ወተትን እለብ። |