Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ምሳሌ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)


ከዝሙት ስለ መራቅ

1 ልጄ ሆይ፥ ጥበቤን ተመልከት፤ ጆሮህም ወደ ቃሌ ያድምጥ፥

2 መልካም ዐሳብን ትጠብቅ ዘንድ በከንፈሮቼ የማዝዝህን ዕወቅ።

3 ከአመንዝራ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና፥ ወደ አመንዝራ ሴት አትመልከት፥ ለጊዜው ጕሮሮህን ያጣፍጣል፥

4 ፍጻሜው ግን እንደ ሐሞት የመረረ ነው፥ ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅም የተሳለ ነው።

5 እግሮችዋም ወደ ስንፍና ይወርዳሉ፥ አረማመድዋም ወደ ሞትና ወደ ሲኦል ያደርሳል። ፍለጋዋ ከኀጢአት ቦታ አይርቅም፥

6 በሕይወት መንገድም አትሄድም። መሮጫዋ ሰንከልካላ ነው፥ የሚታወቅም አይደለም።

7 አሁንም ልጄ ሆይ፥ ስማኝ፥ ቃሌንም የተናቀ አታድርግ

8 መንገድህን ከእርስዋ አርቅ፥ ወደ ቤቷም ደጅ አትቅረብ፥

9 ሕይወትህን ለሌላ እንዳትሰጥ፥ ንብረትህንም ምሕረት ለሌላቸው፤

10 ባዕዳን በሀብትህ እንዳይጠግቡ፥ የድካምህም ፍሬ በባዕድ ሰው ቤት እንዳይገባ።

11 ሰውነትህ በደከመ ጊዜ፥ ኋላ ትጸጸታለህ፥

12 እንዲህም ትላለህ፦ “እንዴት ትምህርትን ጠላሁ! ልቤም ከተግሣጽ እንዴት ራቀ!

13 የአስተማሪዎቼንም ቃል አልሰማሁም፥ ጆሮዎቼንም ወደ አስተማሪዎቼ አላዘነበልሁም።

14 በማኅበርና በጉባኤ መካከል፥ ወደ ክፉ ሁሉ ለመድረስ ጥቂት ቀረኝ።”

15 ከማድጋህ ውኃ፥ ከምንጭህም የሚፈልቀውን ውኃ ጠጣ።

16 ከምንጮችህ ውኆች ወደ ሜዳ አይፍሰሱ። ውኃዎችም ወደ አደባባዮች አይሂዱ፥

17 ለአንተ ብቻ ይሁኑ፥ ከአንተ ጋር ላሉ እንግዶችም አይሁኑ።

18 የውኃ ምንጭህ ለአንተ ይሁንልህ፤ ከልጅነት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ።

19 በዋሊያና በውርንጭላ ፍቅር፥ ከሚስትህ ጋር ተፋቀር፥ የፍቅርዋ ሞገስ ያርካህ፥ ለአንተ ትሁንህ፥ ሁልጊዜም ከአንተ ጋር ትኑር፤ በዚች ፍቅር ስትፋቀር ብዙ ትሆናለህ።

20 ልጄ ሆይ፥ ከሌላዪቱ ሴት ጋር አትኑር፤ የአንተ ወዳልሆነችውም እጅህን አትዘርጋ።

21 የሰው መንገድ በእግዚአብሔር ዐይኖች ፊት ነውና፥ አካሄዱንም ሁሉ እርሱ ይመለከታልና።

22 ኀጢአት ሰውን ያጠምዳል፥ ሁሉም በኀጢአቱ ልባብ ይታሰራል።

23 እርሱ ከሰነፎች ጋር ይሞታል፤ ከስንፍናውም ብዛት የተነሣ ሕይወቱ ይጣላል፤ ስለ ስንፍናውም ይጠፋል።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች